Fana: At a Speed of Life!

የምዕራብ ወለጋ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአሸባሪውን ሸኔና የሌሎች ፀረ ሰላም ቡድኖችን ሴራ እናመክናለን አሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአሸባሪውን ሸኔና የሌሎች ፀረ- ሰላም ቡድኖችን ሴራ ለማምክናን እንሰራለን ሲሉ የምዕራብ ወለጋ ወጣቶች ገለጹ፡፡
 
“ምክንያታዊ ወጣቶች” በሚል መሪ ሀሳብ የወጣቶች የምክክር መድረክ ዛሬ በጊምቢ ከተማ ተካሂዷል፡፡
 
በዞን ደረጃ በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የአሸባሪዎች ሴራ ለመመከት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
 
ሁሉም ወጣት የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር ከመንግስት የፀጥታ አካላት ጋር በመሰለፍ የአሸባሪውን ሸኔና የሌሎች ፀረ ሰላም ቡድኖችን የጥፋት ድርጊት መመከት የነገ ሀገር ተረካቢ ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
 
ወጥቶ መግባትና ሰርቶ መለወጥ የሚቻለው የዜጎች ሰላም ሲረጋገጥ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
በተለይ የሀገር ሰላምና እድገትን አጠናክሮ በማስቀጠል ሂደት እንደ ወጣት ያለባቸውን የዜግነት ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት፡፡
 
“አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን የጠላት እኩይ ተግባርና ሴራ ለማምከን የዞኑ ወጣቶች በአንድነት እንቆማለን ያሉት ወጣቶች÷ሰላምና እድገት በሀገሪቱ እንዲረጋገጥ ለውጡን የመጠበቅ ሃላፊነት የወጣቱ ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
 
በአሁኑ ወቅት በወጣቱ መስዋእትነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከሀገር ውስጥ ጋላቢዎቹና ከውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋት ሴራን እየፈጸመ ያለውን ሸኔና ግብረ አበሮቹን ለማምከን በሚሰራው ስራ ላይ ድርሻችንን እናጠናክራለን ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
 
“ወጣቱ በየትኛውም የጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል በትግሉ የመጣውን ለውጥ ማስቀጠልና የሚፈለገውን ግብ እንዲያሳካ መስራት ይጠበቅበታል” ነው ያሉት።
 
በምዕራብ ወለጋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሊላ ተረፈ በበኩላቸው÷ለውጡ ያልተዋጠላቸው የኢትዮጵያን መፍረስ የሚፈልጉ ቡድኖች ያላደረጉት ሙከራ የለም ብለዋል።
 
የለውጡ ባለቤት የሆነው ወጣቱ ሃይል አንድነቱን በማጠናከር ዛሬም የሀገር አፍራሾችን ሴራ በማክሸፍ ሰላምንና ልማትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
 
የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
 
ወጣቶቹ ሰሞኑን በዞኑ በቶሌ ቀበሌ በአሸባሪው የሸኔ ቡድን የተፈፀመውን የንጹሃን ግድያ እንደሚያወግዙም ተናግረዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.