Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

ቫይረሱን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ብሄራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ስራውን ገምግሟል።

በዚህ ወቅትም ቫይረሱ እስካሁን ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ባይገባም የክትትልና የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

ቁጥጥሩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በ30 የየብስ በሮች እየተደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ቫይረሱ ምናልባት በኢትዮጵያ ቢከሰት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እጥረት ሊያጋጥም ስለሚችል፥ በሃገር ውስጥ ተመርቶ ለውጭ ገበያ ይቀርብ የነበረው ጭምብል እንዲቆም ተደርጓልም ነው የተባለው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የህክምና ተቋማት ዝግጁ የተደረጉ ሲሆን፥ በአዲስ አበባ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ይህን ህክምና ብቻ እንዲሰጥ ተለይቷል።

ሆስፒታሉ በአንድ ጊዜ 300 ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፥ በሂደት አቅሙ በእጥፍ የሚጨምር ነው ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በቢሾፍቱ የመከላከያ ሆስፒታል ለዚህ ስራ ተለይቶ የተዘጋጀ ሲሆን፥ በክልሎች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሉባቸው አካባቢዎችም የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ቫይረሱ ዓለም ላይ ከተከሰተ ወዲህም በኢትዮጵያ ሊካሄዱ ታስበው የነበሩ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች መሰረዛቸውም ታውቋል።

በአላዛር ታደለ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.