በ11 ወራት ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል – የደቡብ ምዕራብ ክልል ገቢዎች ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 11 ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ2014/15 የግብር ከፋዮች የግብር አከፋፈል ንቅናቄ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ በንቅናቄው ላይ እንደገለጹት÷ በ2014 ዓ.ም በክልሉ በተከለሰው ዕቅድ መሰረት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በ 11 ወራት ውስጥም ለመሰብሰብ ከታቀደው 2 ነጥብ 58 ቢሊየን ብር 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ጠቁመው÷ከተሰበሰበው ገቢም አብዛኛው ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ሰራተኞች የተገኘ ነው ብለዋል፡፡
በ2014/2015 የግብር መክፈያ ወቅት ከሀምሌ እስከ ጥቅምት ከደረጃ ሐ፣ ለ እና ሀ ግብር ከፋዮች 238 ሚሊየን 780 ሺህ 588 ብር ለመሠብሰብ መታቀዱንም ነው ወይዘሮ ህወት አሰግድ የተናገሩት፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግስት ተጠሪ አቶ ጸጋዬ ማሞ÷ ክልሉ በሀብቱ መጠቀም እንዲችል ጠንካራ የግብር አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መሠረተ ልማትን በማሟላትና ኢንቨስትመንትን በመሳብ ክልሉን ማልማት የሚቻለው ካለው ሀብት በአግባቡ ገቢን መሠብሰብ ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
በተስፋዬ ምሬሳ