Fana: At a Speed of Life!

በአማራና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችል የሰላም ፎረም ተመሠረተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችል አካባቢያዊ የሰላም ፎረም ተመሠረተ፡፡

ፎረሙ የተመሰረተው በወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ኢ ኤል አይ ዲ ኤ (ELiDA) ከተባለና በትምህርት፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በገቢ ማስገኛ፣ በዴሞክራሲ፣ በባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ ከሚሰራ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበራት ድርጅት ጋር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

በምስረታው ላይ የአፋር ክልል ዞን 5 ፣ የደቡብ ወሎ ዞንና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ኃይሉ ÷ የአማራና የአፋር ህዝብ የተዋለደ፣ የተዋደደና በባህልና እሴት የተሳሰረ መሆኑን አንስተው አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በሽምግልና ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አወል ሰይድ በበኩላቸው÷ ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ተቋማት ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለአካባቢው ሰላም ዋነኛ መፍትሄ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢ ኤል አይ ዲ ኤ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዚነት ይመር በበኩላቸው÷ የአማራና የአፋርን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ በቅንጅት እንሰራለን ማለታቸውን ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.