Fana: At a Speed of Life!

ጠርዝ የረገጡ ሐሳቦች ወደ መሀል እንዲመጡ እና ዜጎች እንዲተባበሩ ማድረግ ይገባል – የሃይማኖት መምህራን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠርዝ የረገጡ ሀሳቦች ወደ መሀል እንዲመጡ እና ዜጎች እንዲተባበሩ ማድረግ እንደሚገባ የተለያዩ የሃይማኖት መምህራን ገለጹ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ ሃይማኖቶች መምህራን ጠርዝ የረገጡ ሀሳቦች ወደ መሀል እንዲመጡ እና ዜጎች እንዲተባበሩ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህ ዓላማም የሃይማኖት አባቶች ኃላፊነት ከፍ ማለት ይገባዋል ብለዋል፡፡

የሁሉም እምነቶች ወርቃማ መርሆዎችን ለሀገራዊ ምክክሩ አጋዥ እንዲሆኑ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ÷ በሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ መተሳሰቦች እና በጋራ የመቆም አስተምህሮዎች ለሀገር እንዲውሉ ማገዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የእስልምና ሃይማኖት መምህር ዑስታዝ ባህሩ ዑመር እና ወንጌላዊ ተሾመ ተስፋዬ በበኩላቸው÷ የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ካላቸው ተሰሚነት አንጻር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ ለሰላምና መረጋጋት ካለው ከፍተኛ ጥቅም አኳያ ትኩረት እንዲሰጠው የሃይማኖት መምህራን ተመሳሳይ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

ስክነትና አስተዋይነት የታከለባቸው ምክክሮች እንዲደረጉ እና ጥላቻ ተወግዶ ይቅር ባይነት እንዲተካ የሃይማኖት አባቶች በየእምነት ተቋማታቸው ሊያስተምሩ እንደሚገባም ነው መምህራኑ የገለጹት፡፡

እውቀት እና ተሰሚነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶች እና መምህራን በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸውም ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል፡፡

በአወል አበራ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.