አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሮቤ ከተማ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መረቁ
የአብዲ ቦሩ የሕጻናት ትምህርት ቤት ዛሬ ከተመረቁት የልማት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ሲሆን÷ በ412 ነጥብ 9 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወጪ የተገነባ ነው፡፡
ትምህርተ ቤቱ 6 ብሎኮች ያሉት ሲሆን÷ 333 ሕጻናትን ተቀብሎ የማስተማር አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡
በዛሬው ዕለት ከተመረቁት ፕሮጀክቶች በ1 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባው የመደ ወላቡ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን÷ 24 ክፍሎች ያሉት እና 2 ሺህ 200 ተማሪዎችን የማስተማር አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በ21ሚሊየን ብር የተገነባው የጀነራል ዋቆ ጉቱን ሐውልት የያዘው አደባባይ ተመርቋል።
ባለፉት ዓመታት ለበርካታ ጊዜ የባሌ ሕዝብ የእኚህን ጀግና መሪ የሚዘክር ሐውልት እንዲሠራ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ “ጀነራል ዋቆ በተከተሉት መርህ መሠረት ዛሬ በልጆቻቸው ሐውልታቸው ቆሞ ተስፋቸውም በልማታቸው እየተመለሰ ይገኛል” ብለዋል።