Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበራቸው አካባቢ የተፈጠረውን ውዝግብ በውይይት እንዲፈቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና ኢጋድ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበራቸው አካባቢ የተፈጠረውን  ውዝግብ በውይይት እንዲፈቱ የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ ጠየቁ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የኢትዮጵያ እና ሱዳን ወታደራዊ ውጥረት ኮሚሽኑን እንደሚያሳስበው ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ከወታደራዊ እርምጃ እንዲታቀቡ የጠየቁት ሊቀመንበሩ፥ ሁለቱ እህተማማች ሀገራት የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ውይይትን እንዲያስቀድሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተከሰተው የድንበር ውዝግብ በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተከሰቱ ያሉ የውስጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ዲፐሎማሲያዊ ጥረቶችን ማደናቀፍ እንደሌለበትም ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል።

በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት እያጋጠማቸው ያለውን የድንበር ውዝግብ በአፍሪካ ህብረት የድንበር መርህ መሰረት ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነው ያሳሰቡት።

በተመሳሳይ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በሀገራቱ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብን ምክንያት ያደረገ ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቅርቧል።

የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በቅርቡ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረው የድንበር ላይ ውጥረት መባባስ  ኢጋድን እንዳሳሰበው ነው የገለፁት።

ሁለቱ ወንድማማች ሀገራት ውጥረቱን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ዋና ፀሀፊው፥ በጉዳዩ ዙሪያ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እንዲከተሉ ጠይቀዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት “የምርኮኛ አያያዝን ባልተከተለ መንገድ ወታደሮቼን ገድሏል” በሚል የሱዳን ጦር የሚያናፍሰው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴር ትናንት መግለፁ ይታወሳል።

በቅርቡ የሱዳን ወታደራዊ ሀይል ከአሸባሪው ህወሃት እና ሰራዊቱን በተለያዩ ጊዜ ከከዱ አመራርና አባላት ጋር ተቀናጅተው የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ሰርገው በመግባት በአካባቢው ሚሊሻና ነዋሪ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ነው ያመለከተው።

ነገር ግን የኢፌደሪ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ባልነበረበት ሁኔታ “ምርኮኞችን ገደለ” በሚል ከሱዳን በኩል ክስ መቅረቡ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ቀድሞ ባወጣው መግለጫ፥ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በመግባት ፀብ ጫሪ ድርጊት የፈፀመው ወገን የሱዳን ጦር ሆኖ ሳለ በሁኔታው ኢትዮጵያን ተጠያቂ ለማድረግ የሚሞከርን የትኛውንም ድርጊት መንግስት እንደማይቀበል ነው ያስታወቀው።

የሱዳን መንግስት ሁነቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች በመቆጠብ የተፈጠረውን ድርጊት ሊያርግቡ የሚችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስድ የኢትዮጵያ መንግስት ተስፋ እንደሚያደርግም መግለጫው ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.