Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ምዕራብ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተመሰረተ፡፡
በክልላዊ የጋራ ምክር ቤት ምስረታ መርሐ ግብሩ ላይ÷ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ ብልጽግና ፓርቲ፣ የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የካፋ ህዝቦች አረንጓዴ ፓርቲ እና ሌሎች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል።
የደቡብ ምዕራብ ክልል መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞ በምስረታው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የክልላችን ሕዝቦች የልማት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
የክልላችን ጉዳይ የሁሉም አካላት ድርሻ በመሆኑ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የካፋ ሕዝቦች አረንጓዴ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አየለ÷ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ክልላዊ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ተስማምተው የጋራ ምክር ቤት መመስረት ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነቶችን በማጥበብ ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ አጀንዳዎችን ቀርጸው ሀገርን ለማሻገር ፍትሀዊ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር እንደሚጠበቅባቸውም ተመላክቷል፡፡
በምስረታው ላይ÷ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ፣ የጋራ ምክር ቤት የውይይት ስርዓት የሚመረበት መተዳደሪያ ደንብና የጋራ ምክር ቤትን በቀጣይ የሚመራ 5 ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተካሂዷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፥ አቶ ሰለሞን አየለን ከካፋ ሕዝቦች አረንጓዴ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ ግርማ ባሻን ከብልጽግና ፓርቲ የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አድርጎ በመሾም ተጠናቋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.