Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ሜካናይዜሽን የልኅቀት ማዕከልን ለማቀቋቋም ከደቡብ ኮሪያ ጋር እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ግብርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ሜካናይዜሽን ለመደገፍ የሚያስችል የልኅቀት ማዕከል ለመገንባት ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያን የግብርና ሜካናይዜሽን የልኅቀት ማዕከል ለማቀቋቋም ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ጋር እየተሰሩ በሚገኙ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ÷ የግብርናው ዘርፍ የአገራችን ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተርና የብልፅግናችን ጠቋሚ መንገድ እንደመሆኑ መጠን ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታት ይበልጥ አጠናክረን በመስራት ስንዴን ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

ይህ የሚሆነውም የግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመደገፍ ማምረት ሲቻል መሆኑን ገልጸው÷ የደቡብ ኮሪያ መንግስትና ህዝብ በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ዘርፍ ለማዘመንና ለመደገፍ ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሶአክ ሂ በበኩላቸው ÷ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ዘርፍ ለማሳደግና ለማዘመን ብሎም የምጣኔ ሀብትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በደቡብ ኮሪያ መንግስት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትም ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ነው የጠቆሙት፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ በረከት ፎርሲዶ ÷ በደቡብ ኮሪያ መንግስት ድጋፍ የሚቋቋመው የግብርና ሜካናይዜሽን የልኅቀት ማዕከል ሦስት የተለያዩ ዋና ዋና ክፍሎችና ተግባራቶች ይኖሩታል ብለዋል፡፡

የግብርና እና የሜካናይዜሽን የልኅቀት ዋና ማዕከል የሚገነባው በአዲስ አበባ ሲሆን÷ በስድስት የተለያዩ ክልሎች ቅርንጫፍ ማዕከላት እንደሚኖሩት መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.