Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

አቶ ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ በተለይም በኢትዮ ሱዳን ድንበር ሰሞናዊ ሁኔታ፣ እየተካሄደ ባለው የሰላም ግንባታ ሂደት፣ ብሄራዊ ምክክር እንዲሁም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ጋር በተያያዘ ገለጻ አድርገዋል።

በዚህ ወቅትም መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው፥ ሱዳንም ውጥረት ከማባባስ እንድትቆጠብና ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ይዘት ለማላበስ የምታደርገውን ሂደት እንድታቆም ጠይቀዋል።

የሀገራቱን ህዝቦች የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያደነቁት አቶ ደመቀ፥ ሀገራቱ ከድንበር ጋር በተያያዘ ያለውን ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱባቸው በርካታ መንገዶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በቅርቡ በኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ድርጊቱ የተቀነባበረ እና የተደራጀው የሱዳን ወታደራዊ ኃይሎች ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር በመሆን የፈጸመው መሆኑንም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለተፈጠረው ግጭት ዕልባት ለመሥጠትም መንግስት ዕርምጃዎችን በቁርጠኝነት እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ለሀገር ሠላም የሚበጅ እርሳቸው በሊቀመንበርነት የሚመሩት በመንግስትና በህወሓት መካከል ውይይት እንዲካሄድ የሚሠራ ኮሚቴ መቋቋሙንም አመላክተዋል፡፡

መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ እየሠራ እንደሚገኝና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ህወሓት ላይ ጫና በማሳደር ከግጭት ቀስቃሽነት ተግባሩ እና ወደ ሌላ ጦርነት ውስጥ ከሚከት ድርጊቱ የሚታቀብበት ሁኔታ እንዲያመቻቹም ጠይቀዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ÷ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሁሉን አቀፍ ውይይት ለማካሄድና ለዘመናት የቆዩ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን መቋቋሙንም ጠቁመዋል፡፡

መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ዕርዳታ እና አቅርቦት እንዲዳረስ መሥራቱ እንዲሁም ከፍተኛ የፖለቲካ ባለሥልጣኖች ከእስር ቤት መለቀቃቸው መንግስት ከህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታላቁን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ በሦስትዮሽ ድርድሩ ላይ አቋሟን ይፋ ማድረጓንና ጉዳዩን ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር በውይይት ለመፍታት ሁልጊዜም ገንቢ ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በገባችበት ጊዜ ሁሉ ላሳዩት አጋርነት ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.