Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሰፋፊ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሳ አስታወቁ፡፡

ክልሉ እንደ ክልል የተደራጀበትን ሁለተኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ሰኔ 27 ቀን 2014 እንደሚያከብርም ተገልጿል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሀገሪቱ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄው ምላሽ አግኝቷል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታትም ህዝቡን ወደ ልማት በማስገባት ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ክልል ሲደራጅ ከህዝቡ ጋር በተደረገ ውይይት ይነሱ የነበሩ የልማት ጥያቄዎች ተለይተው ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ሰፊ ጥረት መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በወቅቱ በቀዳሚነት ሲነሳ የነበረውን የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ ከ600 ሚሊየን በሚበልጥ ወጪ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን መንገድ መገንባቱን ጠቅሰዋል።

የመንገድ ግንባታዎቹ ቀበሌን ከቀበሌ፣ ከወረዳና ከክልል የሚያገናኙ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሀ ሽፋኑን ለማሳደግ በተከናወነው ስራም 37 በመቶ የነበረው የክልሉ የውሀ ሽፋን 49 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የኃይል አቅርቦትን ለማመቻቸት በተደረገው ጥረትም ሰፋፊ የኤሌክትሪክ አስተላላፊ መስመሮች መዘርጋታቸውን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በጤናው ዘርፍ አዳዲስ የጤና ተቋማት ግንባታዎች፣ ነባርን የማጠናከርና በግብአት የማደራጀት ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡

ሀገራዊ አንድነቱን ለማስቀጠል ክልሉ በመደገፍ ያከናወናቸው ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ኢትዮጵያውያን ተከባብረው የሚኖሩበት ክልል ለማድረግ የተሰራው ስራም ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ያለው ሠላም ለቱሪዝም ተመራጭ እንዳደረገውና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች እንዲመጡ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያጠናከር አመልክተው፤ የተገኙ ድሎችን ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ የክልሉ የምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.