Fana: At a Speed of Life!

ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እቅድ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ሚና በመወጣት አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እቅድ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ሚና በመወጣት አሻራውን እንዲያሳርፍ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ጥሪ አቀረቡ፡፡

“አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና በየካ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በይፋ ተጀምሯል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስኮ አዲስ ሰፈር አካባቢ በተካሄደው መርሐ-ግብር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሽታዬ መሃመድ እና ሌሎች የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ነዋሪዎች መሳተፋቸውን ከክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚሁ ወቅት ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በተያዘው አመት በመዲናዋ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለእቅዱ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ሚና በመወጣት አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ሽታዬ መሃመድ በበኩላቸው÷ ህዝቡን በማሳተፍ እንደ ክፍለ ከተማ ከ400 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው ችግኞች ከተተከሉ በኋላ ተንከባክቦ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በየካ ክፍለ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በይፋ የተጀመረ ሲሆን÷ 750 ሺህ ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ተገልጿል፡፡

በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መራጊያው ተበጀን ጨምሮ የክፍለ ከተማው ከተማ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና ነዋሪዎች መሳተፋቸውን የየክፍለ ከተሞች ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.