Fana: At a Speed of Life!

‘ፊያስ’ በተባለ የኦንላይን ማጭበርበሪያ ዘዴ ገንዘባቸውን ያጡ ሰዎች ለሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ‘ፊያስ’ በተባለ የኦንላይን ማጭበርበሪያ ድርጊት ገንዘባቸውን ያጡ ሰዎች ለሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ጥሪ አቀረበ፡፡

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ እንደገለጹት÷ ‘በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ እናደርጋችኋለን’ በሚል የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የማጭበርበር ተግባራት የሚፈፅሙ አካላት ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

‘ፊያስ’ እየተባለ የሚጠራው የኦንላይን ድርጊት እንደ ሌሎች በማህበራዊ እና በኦንላይን ሚዲያዎች በመጠቀም ከሚፈፀሙ የማጭበርበሪያ ድርጊቶች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ኃላፊው ጠቁመዋል።

ይህን ተግባር የሚፈፅሙ አካላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋማ እናደርጋችኋለን በሚል እና የተለያዩ የሚያጓጉ ምክንያቶችን በማቅረብ ሰዎችን እያጭበረበሩ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ማህበረሰቡም በአጭር ጊዜ ለመለወጥ በሚል ሕጋዊነቱን ሳያረጋግጥ እና በሚያውቋቸው ሰዎች በመሳብ የወንጀሉ ሰለባ እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

በ ‘ፊያስ’ ተጭበረበሩ ሰዎች ባደረሱት ጥቆማ መሰረት የተለያዩ የክፍያ መንገዶችን በመጠቀም÷ የሰዎችን ገንዘብ የሰበሰቡ አካላትን ሁኔታው እስከሚጣራ ድረስ የባንክ ሂሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ የሚደረግበት አግባብ ይኖራል ብለዋል፡፡

አጠቃላይ የወንጀል ምርመራ ሂደቱ ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑ ጉዳዩ ተጣርቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝርዝር መረጃዎችን ማቅረብ እንደማይቻልም ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡ የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚሠሩ ሥራዎች ላይ ሲሳተፉ አብረው የሚሰሩት አካል በኢትዮጵያ ሕጋዊ እውቅና ያለው መሆኑንና ትክክለኛ ማንነት እንዲሁም አድራሻ ያለው መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ መጠቆማቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ያለምንም ስራ እንደቀልድ የሚሰበሰብ ሃብት ሊኖር እንደማይችል በመገንዘብ መሰል ስራዎች ላይ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ እና ህብረተሰቡ ከመሰል የማጭበርበር ተግባራት ራሱን እንዲጠብቅም አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.