Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ከወሰደው የግጭት ማቆም ውሳኔ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል የሚጓጓዘው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል – ተመድ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ በተገቢው ሁኔታ እንዲደርስ ከወሰደው የግጭት ማቆም ውሳኔ በኋላ ወደ ክልሉ የሚጓጓዘው የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታወቀ፡፡

ከፈረንጆቹ ሚያዝያ 1 ቀን ጀምሮ ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚጓጓዘው የምግብ ድጋፍ እየደረሰ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል፡፡

በዚህም የዓለም የምግብ ፕሮግራም በወር 5 ነጥብ 9 ሚሊየን ሰዎችን መመገብ የሚችል በቂ ምግብ ማቅረቡን ተመድ በትዊተር ገጹ አስታወቋል።

የፌደራል መንግስት ከወራት በፊት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ ወደ ክልሉ እንዲደርስ በማሰብ የግጭት መቆም ውሳኔ መወሰኑ ይታወሳል።

በሌላ በኩል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ኢትዮጵያ ድህነትን በመቀነስ እና በመሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ መሰረተ ልማትን በማሟላት ትልቅ እመርታ ማስመዝገቧን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ የደረሰባትን ችግር በመቋቋም በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በ2025 ሀገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑንም አውስቷል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማገዝ በተለይም በገጠሩ አካባቢ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እርዳታ የሚያቀርበውን የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም መደገፉን እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡

ዜጎች አሁን ካሉበት አስቸጋሪ የእለት እርዳታ እንዲላቀቁ እና ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመላክቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች በመለየት ያለ ቅድመ ሁኔታ የምግብ እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቀው።

በሀገሪቱ የተጀመረውን የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር እና አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮች ገቢ ለማሳደግ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የገለጸው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.