Fana: At a Speed of Life!

በፍርድ ቤቶች የፍትህ መጓተትን እና የፍርድ መዛባትን የሚፈጥሩ የሙስና ስጋቶች መታየታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍርድ ቤቶች የፍትህ መጓተትን እና የፍርድ መዛባትን የሚፈጥሩ የሙስና ስጋቶች እየተስተዋሉ መሆኑን የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ በፍርድ ቤቶች ላይ የሚታዩ የሙስና ስጋቶችን አስመልክቶ ያስጠናውን ጥናት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

በጥናቱ ግኝት መሠረት በፍርድ ቤቶች የፍትህ መጓተት እና የፍርድ መዛባትን የሚፈጥሩ የሙስና ስጋቶች ታይተዋል ተብሏል።

ከተገልጋይ ጋር ያለአግባብ የሆነ ግንኙነት መፍጠር፣ የአንዳንድ ዳኞች የሥነ ምግባር መጓደል፣ የዳኝነት ስራውን በግልፅ ችሎት አለማከናወን፣ የምስክሮች ቃል ተቆርጦ እንዲቀርብ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች የሙስና ስጋቶች መኖራቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ጥናቱ የተደረገው በፌዴራል እንዲሁም በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በተመረጡ ፍርድ ቤቶች በተወሰዱ ናሙናዎች ሲሆን÷ ከፍርድ ቤቶች የተገኘ ሰነድ፣ ከአመራሮች፣ ሠራተኞችና ከሥነ ምግባር መኮንኖች መረጃ ተሰብስቧል፡፡

በጥናቱ ግኝት መሰረት መዝገብ በመደበቅ እና በማጥፋት የማፈላለጊያ ገንዘብ መጠየቅ ከታዩ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ ተብሏል።

ኮሚሽኑ በፍርድ ቤቶች ላይ የሚታይ የሙስና ስጋትን አስመልክቶ ባስጠናው ጥናት የመፍትሔ ሀሳቦችም የተጠቀሱ ሲሆን÷ የሥነ ምግባር ግድፈት በሚፈፅሙ ዳኞች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባና መዝገቦች ኦዲት መደረግ እንዳለባቸውም ነው የተጠቆመው፡፡

በሞሊቶ ኤልያስ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.