Fana: At a Speed of Life!

ግብፅና የህወሓት ተላላኪዎች ኢትዮጵያንና ሱዳንን ለመከፋፈል  እያሴሩ ነው – የፖለቲካ ተንታኝ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅና የህወሓት ተላላኪዎች ኢትዮጵያንና ሱዳንን ለመከፋፈል  እያሴሩ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኙ  አንድሪው ኮሪብኮ ገለፀ።

 

ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን የሚተነትነው እና በተለይም የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ ተደጋጋሚ ትንታኔዎችን የሚፅፈው አሜሪካዊው አንድሪው ኮሪብኮ፥  በፅሁፉ ካይሮ የከፋፍለህ ግዛ አካሄድን በመከተል ሱዳንን እና ኢትዮጵያን በመለያየት የራሷን የበላይነት በሰፊው ቀጣና ላይ ለማስፈን ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን ያመለክታል።

 

“በዚህም ሱዳናውያን የግብጽን ሴረኝነት ቢጠረጥሩም ሀገሪቱ ከጀርባቸው ለመውጋት እያሴረች መሆኑን ግን ገና አልተገነዘቡም” ብሏል።

 

ዘ ኢኮኖሚስት ባለፈው ግንቦት ወር መገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ጦርነት ለመቀስቀስ በማሰብ የሀሰት ዜናዎች ማሰራጨቱን ያስታወሰው ተንታኙ፥ ይህ አድሎ ያለበት የተቋሙ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ በሀገራቱ የድንበር ላይ ግጭት ያወጣው ዘገባ “የሴራ ንድፈ ሃሳብ” ያዘለ መሆኑንም አንስቷል።

 

ይህም ሱዳን በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ከከፈተችው የጦርነት ቅስቀሳ በፊት እንደነበር ነው የሚያስረዳው፡፡

 

የሱዳን ወታደሮች ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው መግታቸውን በመጥቀስም፥  በሁለቱም ወገኖች ጉዳዩ “አወዛጋቢ” እንደሆነ አመልክቷል።

 

ይህን ተከትሎም ሱዳን በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጠብ ጫሪ በመሆን ሀገራቱ ወደ ጦርነት አፋፍ እንዲደርሱ ማድረጓንም ነው የገለጸው።

 

ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳናውያን ባስተላለፉት መልዕክት የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት ማንሳታቸውን በማንሳት፥ ሶስተኛ ወገን በማስገባት ከፋፍለው እንዲገዙ መፍቀድ እንደማይገባ ማስጠንቀቃቸውንም ያስታውሳል።

 

በዚህም ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በሰላማዊ መንገድ ልዩነቶቻቸውን በጋራ በመፍታት ዜጎቻቸውን በልማት ላይ በማሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋልም ነው ያለው።

 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መግለጫ የተነሳው ሀሳብ ላይ ተግባራዊነት መታየት ይኖርበታል የሚለው ተንታኙ፥ ዲፕሎማሲያዊ አተያዩ ግን ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን ይገልጻል።

 

“እንደ እውነቱ ከሆነ እየሆነ ያለው ግብፅና በአሸባሪነት የተፈረጁ የወያኔ ተላላኪዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ሽፋን በድብቅ በሚቀርብላቸው ድጋፍ፥ ኢትዮጵያን እና ሱዳንን ለመከፋፈል እና ለመግዛት እያሴሩ ነው” ሲልም ያስረዳል።

 

በዚህ ሂደትም የራሳቸውን ድብቅ አላማ ለማሳካትና ብሎም የአፍሪካን ቀንድ በስውር ጦርነት ለማተራመስ እቅድ በማውጣት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑም ነው የሚገልጸው።

 

ይህ የሚደረገው በአሜሪካ በሚመሩት ምዕራባውያን ትዕዛዝ መሆኑን ያነሳው አንድሪው ኮሪብኮ ፥ ኢትዮጵያ እንደ ግብፅና እንደ ባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት ባሉ የውጭ ድርጅቶች ድጋፍ ባይኖራትም ሉዓላዊነቷን ታስጠብቃለችም ነው ያለው።

 

ግብፅ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማረጋገጥ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመገንባት ሉዓላዊ መብቷን ፖለቲካዊ መልክ ማላበሷን ያነሳው ባለሙያው ፥ ራሷ ካይሮ ግን የኤሌክትሪክ ሃይል ወደውጭ እየላከች እንደሆነና ኢትዮጵያን ለማተራመስ የምታሴረው ለዚህ እንደሆነም ያስረዳል።

 

ግድቡ እንደ ሱዳን እና ግብፅ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ስጋት እንደማይፈጥር እና ይልቁንስ በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል እንደሆነ ማየት መቻሉንም ጠቅሷል፡፡

 

ዘገባው አሸባሪው ህወሓት እና ግብጽ የምትዘውራቸው ሱዳናውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽሙት ትንኮሳና ጥቃት፥ በግብጽ ብሎም በአሜሪካ እና ምዕራባውያን ድጋፍ ሰጪነት በቀጣናው የሚያካሂዱት የእጅ አዙር ጦርነት አካል መሆኑን አትቷል፡፡

 

ሰሞኑን ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው የጠብ ጫሪነት ድርጊት ከሶስተኛው የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጋር መገጣጠሙም ግብጽ እና ደጋፊዎቿ በኢትዮጵያ ላይ ያሰቡትን  ሴራ አመላካች መሆኑን  አጽንኦተ ሰጥቷል፡፡

 

ከዚህ ባለፈም የሱዳን አደገኛ ግጭት ቀስቃሽ ድርጊት አሁን ላይ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ ሀገራት ጫፍ የረገጠ ልዩነት በፈጠሩበት ወቅት መፈጸሙ ክስተቱ ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ ያደርገዋልም ነው ያለው።

 

የዚህ ትልቅ ሴራ ዋና ግብም ሶስተኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት እንዳይሳካ፥ “ቦሲኒያ በተከፋፈለችበት መንገድ”  ኢትዮጵያን እንድትዳከም ማድረግ መሆኑንም አስረድቷል።

 

አሸባሪው ህወሓት እና ሱዳን በግብጽ መሪነት በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት የእጅ አዙር ጦርነትም አሁን ላይ የተከሰተውን ዓለም አቀፋዊ ቀውስ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በቀቢጸ ተስፋ ምኞት የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ያለመ መሆኑንም አውስቷል፡፡

 

የሱዳን ህዝቦች፣ ኢትዮጵያ የምንግዜም ወዳጅ ሀገር እንጂ ጠላታቸው አለመሆኗን መገንዘብ  አለባቸው ያለው አንድሪው ኮሪብኮ፥ በሀገራቱ ግንኙት ጣልቃ የሚገቡ አካላት የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ውድቀት የሚመኙ እና የሚያፋጥኑ መሆናቸውን መርሳት እንደሌለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

 

በሌሎች የውጭ ሀይሎችም ጭምር የሚቀናበረውን ይህን ሴራ ግብጽ በተላላኪዋ ህወሓት እና ቀጥተኛ ትዕዛዝ በምትሰጠው የሱዳን መንግስት አማካኝነት በቀጥታ እየመራችው መሆኑንም አመላክቷል፡፡

 

የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅቡልነት ያለው ፖሊስ እና ስትራቴጂ መተግበር እንደሚገባ የሚያትተው ተንታኙ፥ የሱዳን ወታደራዊ አመራሮችም በጀመሩት የእጅ አዙር ጦርነት እና የተላላኪነት ሴራ ምንም አይነት ጥቅም ሊያገኙ እንደማይችሉ በመገንዘብ አካሄዳቸውን በድጋሜ ማጤን እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡

 

ሁልጊዜም ቢሆን አሸባሪውን ህወሓት መደገፍ መጥፎ ሃሳብ መሆኑን ያነሳው አንድሪው ኮሪብኮ፥ ጌቶቻቸው እንደሚያስቡት መቼም ቢሆን መንግስትን መጣል እንደማይሳካላቸውም ነው የገለጸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.