Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች ከድጎማ በጀትና ከጋራ ገቢዎች የሚያገኙት የገቢ ድርሻ እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ክልሎች ከድጎማ በጀትና ከጋራ ገቢዎች የሚያገኙት የገቢ ድርሻ እየጨመረ መምጣቱን ገለጹ፡፡

አፈ ጉባዔው በክልሎች መካከል የሚታየው ዕድገት ያልተመጣጠነ መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አቶ አገኘሁ ይህንን ያሉት ÷ በአዳማ ከተማ እያተካሄደ ባለው በበይነ መንግሥታት የፊስካል ግንኙነቶች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመምከር በተዘጋጀው መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡

አፈ ጉባኤው አያይዘውም የፌዴራል ተቋማት ወደ ክልሎች የሚተላለፉ ውስን ዓላማ ያላቸው በጀቶች እና የፌዴራል መሠረተ ልማት ዝርጋታ በአሠራራቸውም ሆነ በስርጭታቸው ፍትሃዊነት ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳባቸው እንደቆየ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ግልፅ፣ አሳታፊና ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋት በሚሠሯቸው ሥራዎች ፍትሃዊነትንና ውጤታማነትን እንዲያረጋግጡ ብሎም ክትትልና ድጋፍ እንዲሠጡ አሳስበዋል፡፡

ኃላፊነት የተሠጣቸው ተቋማትም የተዘረጉት አሠራሮች በትክክል ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ማረጋገጥ ያስችላቸው ዘንድ ደንብ ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡

ከተለያዩ ሀገራት የተገኙትን ተሞክሮዎች መሠረት በማድረግ ፣ በሀገራችን ፍትሃዊና ውጤታማ የበይነ መንግስታት ፊስካል ግንኙነቶችን ለማሳለጥ የሚያግዝ ሙያዊ ነፃነትና ብቃት ያለው ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት እውን ለማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሀገራችን ግልጽ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ የፊስካል ሽግግር ሥርዓቶች እንዲዘረጉ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ምክር ቤቱ ለብቻው ውጤት ማምጣት ስለማይችል ሁለቱ ምክር ቤቶች በተቀናጀ መንገድ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው በአጽንኦት መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.