Fana: At a Speed of Life!

በርካታ የውጭ ሃይሎች ሃገራችንን ለማዳከም ሰፊ የውክልና ጦርነት አውዶች መክፈታቸውን በመገንዘብ ህዝባችን ሊያከሽፈው ይገባል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ የውጭ ሃይሎች ሃገራችንን ለማዳከም ሰፊ የውክልና ጦርነት አውዶች በመከፈታቸው የእነዚህን ሃይሎች ሴራ ህዝባችን በመገንዘብ ሊያከሽፈው እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የ8ኛ ዕዝ በግዳጅ አፈፃፀማቸው ብልጫ ላሳዩ የሠራዊት ክፍሎችና አባላት የሜዳይ እና ዕውቅና መስጠት ስነ ስርዓት አከናውኗል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና፣ የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ አወል አርባ፣ ጄነራል መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ሽልማት በመስጠት የስራ መመሪያ ንግግር ያደረጉት የጥቁር አንበሳ ጀግና ከፍተኛ ሜዳይ ተሸላሚና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ በአሁኑ ሰዓት በርካታ የውጭ ሃይሎች ሃገራችንን ለማዳከም ሰፊ የውክልና ጦርነት አውዶች መከፈታቸውን አንስተዋል፡፡

የእነዚህን ሃይሎች ሴራ ህዝባችን በመገንዘብ ሊያከሽፈው ይገባልም ብለዋል።

የ8ኛ ዕዝ የሰራዊት አመራርና አባላት በፈፀሙት ገድል አገር ከተደቀነባት የመፍረስ አደጋ መታደግ በመቻላችሁ ኩራት ሊሰማችሁ ይገባልም ነው ያሉት።

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሃጂ አወል አርባ ፥ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የተንቀሳቀሰበትን ሂደት አስታውሰው ይህ ቡድን ለዳግም የክህደት ተግባር ከመንቀሳቀሱ በፊት ደጋግሞ ሊያስብበት ይገባል ብለዋል።

የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮለ ፥ ዕዙ ከተቋቋመ አጭር ግዜ ቢሆንም የተዋጊውንና የድጋፍ ሰጭ ክፍሎችን አቅም በመገንባት ለሌሎች እዞች አጋር ክንድ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ዕዙ ለ3ኛ ደረጃ ሜዳይ ምርጥ አዛዥ 16፣ ለ3ኛ ደረጃ ምርጥ ተዋጊ 11፣ ለ3ኛ ደረጃ ድጋፍ ሰጭ 26፣ ለምርጥ አሃዱ 4፣ ሁለተኛ ደረጃ ሜዳይ ለምርጥ አዛዥ 31፣ ለምርጥ ተዋጊ 16፣ ለምርጥ ድጋፍ ሰጭ 10፣ ለምርጥ አሃዱ 2 ሜዳልያ ተሸልሟል።

የ8ኛ ደቦል ዕዝ በዕለቱ አርማውንና መዝሙሩን በክብር እንግዶች ማስመረቁን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.