Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለስደተኞች እና ስደተኞችን በሚያስተናግዱ አካባቢዎች ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የ180 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች እና ስደተኞችን በሚያስተናግዱ አካባቢዎች ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የ180 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ፡፡

ድጋፉ በዋናነት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞችና በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገውን መሰረታዊ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል የሚረዳ ነው።

ከዚህ ባለፈም ኑሯቸውን ማሻሻል የሚችሉባቸውን ዕድሎች ለማስፋትና ምቹ ከባቢያዊ ሁኔታን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ይውላልም ነው የተባለው።

በድጋፉ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 1/3 ያህሉ ስደተኞች መሆናቸውን የባንኩ መረጃ ያመላክታል።

በአፍሪካ ቀንድ ለተፈናቃዮች ድጋፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮ በጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ ውስጥ ከ5 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሰዎች ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል።

ይህ ፕሮጀክት ወሰኑን በማስፋት በስደተኞች መጠለያ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በመስራትና የመንግስት የስደተኞችን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ተገልጿል።

ስደተኞች በድጋፉ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሲሆኑ ፥ ዋና ትኩረቱ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አቅም በማጎልበት በአካባቢያዊ ልማት እቅድ ውስጥ አብረው እንዲጓዙ ማድረግን ያለመ ነው ተብሏል።

በዚህም ፕሮጀክቱ ለስደተኞች እና ስደተኞችን ለሚቀበሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብአዊ ድጋፍን እንደሚያደርግ በዓለም ባንክ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ቀጠናዊ ግንኙነት ዳይሬክተር ቡቴይና ጉርማዚ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ስደተኞችን በመቀበል መቆየቷ የተገለጸ ሲሆን ፥ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚመጡ ወገኖች የምትሰጠው ምላሽ የሚደነቅ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የመጡ ሲሆኑ ፥ በቀጠናው አለመረጋጋት ምክንያት ተፈናቅለው ወደሀገሪቱ የሚገቡ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ፕሮጀክቱ ለስደኞች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በስደተኞች መጠለያ አካባቢ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በራሳቸው እንዲተማመኑ እና በሰብአዊ እርዳታ ላይ ጥገኝነትን እንዲቀንሱ ለማድረግ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ያበረታታል ተብሏል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.