Fana: At a Speed of Life!

በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ዛሬ ይመረቃል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ዛሬ ይመረቃል፡፡
ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተካሄደ ሲሆን÷ በቀን 86 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ ፕሮጀክት የከተማ አስተዳደሩን በቀን ውሃ የማምረት አቅም ከ674 ሺህ ወደ 760 ሺህ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡
16 ጥልቅ ጉድጓዶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው 10 የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታን ያካተተ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የ12 ኪሎ ሜትር ዋና የውሃ መስመር፣ 72 ኪሎ ሜትር የውሃ ማሰባሰቢያ መስመር፣ 99 ኪሎ ሜትር የስርጭት መስመር ዝርጋታ፣ ሁለት ግዙፍ የግፊት መስጫ ጣቢያዎች እና 38 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድን ያቀፈ ፕሮጀክት መሆኑን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች እና በጉድጓዶቹ አካባቢ የሚሰሩ የሲቪል ስራዎችንም የያዘ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከ85 በመቶ በላይ ውሃ የሚያገኘው ከፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን እንደመሆኑ÷ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በዚህ ሶስት አመት ውስጥ በልዩ ዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች እና የገጠር ቀበሌዎች 30 መለስተኛ የውሃ ጉድጓዶች፣ 37 የመጸዳጃ ቤቶች እና 105 ለህብረተሰቡ እና ለውሃ የሚሆን የመዳረሻ መንገድ ሰራዎች እየተሰሩ እንደመገኙ አስተዳደሩ አስታውቋል።
በዛሬው ዕለት የሚመረቀውን የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የውሃ ፕሮጀክትም÷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የምክር ቤት አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ጎብኝተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.