Fana: At a Speed of Life!

በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባውን የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባውን የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት የውሃ ፕሮጀክት ዛሬ መረቁ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የአዲስ አበባን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የምናሻሽለው እንዲህ ያሉ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ነው ብለዋል።

የተጠናቀቀው የውሃ ፕሮጀክት በመጠጥ ውሃ ችግር ሲሰቃይ የነበረውን የአዲስ አበባ ነዋሪ ችግር እንደሚያቃልል ጠቅሰው÷ ፕሮጀክቱ የሚለማበት አካባቢ ነዋሪዎችን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነውም ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት መጠናቀቁ ድሉን ድርብ ያደርገዋልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባና አጎራባች ሕዝቦች አንዱ ያለሌላው መኖር አይችሉም ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ የልማት ስራዎችንም ስናስብ አብሮ መልማትንና የጋራ ተጠቃሚነትን በአብሮነትና በመከባበር የጋራ እሴቱንም በመገንባት ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

የበረኽ ወረዳ አርሶ አደሮች ይህ የውሃ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን ከፍተኛ ትብብር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የንፁሃን ዜጎችን ህይወት የሚነጥቁ እኩይ ምግባር ላይ የተሰማሩ ቡድኖችን በጋራ ማውገዝ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ በበኩላቸው÷ የከተማ አስተዳደሩ እየጨመረ የመጣውን የውሃ ፍላጎት ችግር ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ተሳትፎ ላደረጉ አካላትም በመርሐ ግብሩ ላይ እውቅና ተሰጥቷል።

ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ግዙፍ የከርሰ ምድር ውሃ እንደሆነና ለ860 ሺህ ዜጎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ የከተማ አስተዳደሩን በቀን ውሃ የማምረት አቅም ከ674 ሺህ ወደ 760 ሺህ ሜትር ኪዩብ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

16 ጥልቅ ጉድጓዶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው 10 የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችም ተገንብተዋል፡፡

የ12 ኪሎ ሜትር ዋና የውሃ መስመር፣ 72 ኪሎ ሜትር የውሃ ማሰባሰቢያ መስመር፣ 99 ኪሎ ሜትር የስርጭት መስመር ዝርጋታ፣ ሁለት ግዙፍ የግፊት መስጫ ጣቢያዎች እና 38 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድን ያቀፈ ፕሮጀክት መሆኑም በምረቃው ወቅት ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ግንባታው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች እና በጉድጓዶቹ አካባቢ የሚሰሩ የሲቪል ስራዎችንም የያዘ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአለምሰገድ አሳዬ

ተጨማሪ  መረጃ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.