Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአፈር መረጃ ቋት ላይ የአይሲቲ ግብርናን ጀመረች

አዲስ አበባ፣ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብር ባለፉት 3 ዓመታት ሲዘጋጅ የቆየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የአፈር መረጃ ቋት ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ኢትዮጵያ በአፈር መረጃ ቋት ላይ የአይሲቲ ግብርና መጀመሯን የማብሰሪያ ሥነ ስርዓት ተካሄደ፡፡
ፕሮጀክቱ በግብርና ሚኒስቴር በአፍሪኮም እና በሲ ኤስ ኤም ቴክኖሎጂ ዋና አዘጋጅነት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ፣ ባዮቨርሲቲ ኢንተርናሽናል እና ዓለም አቀፍ የትሮፒካል ግብርና ማዕከል ትብብር የተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ አብረሃ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋስትና የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል ቁልፉ ተግባር መሆኑን ጠቁመው÷ ምርታማነትን ለማሻሻል ደግሞ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ይህን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ተግባር ላይ በማዋል በግብርና ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚቻል መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት ፡፡
ከዚህ በፊት በሀገራችን ሲሰራበት የነበረው የአፈር መረጃ ቋት አናሎግ በመሆኑ መረጃዎች የተበታተኑ፣ የማይጣጣሙ እና ካርታ ጠቆሚ ያልሆኑ መሆናቸውን አውስተው÷ይህም ያለውን የአፈር መረጃ ለማከማቸት፣ ለማተሳሰር፣ ለማዘመን እና ለመጠቀም እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
ይህን በመገንዘብ የኢትዮጵያ መንግስት ከሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ብሄራዊ የአፈር መረጃ ስርዓት ለመዘርጋት ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።
የአፍሪኮም መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ዘይኑ በበኩላቸው÷ ቴክኖሎጅው ከዳሰሳ ጥናቱ የተገኙ መረጃዎችን በአንድ ማዕከል በማጠናከር ፈጣን የመረጃ ልውውጥን የሚያመቻች እና የአፈር ናሙናን በመፈተሽ የአፈር ባህሪያትን እና ዓይነቶችን በካርታ እና በዕይታ ማሳየት ያስችላል ብለዋል፡፡
በግብርና ሚስቴር የአፈር ሃብት መረጃና ካርታ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ንጋት ተሰማ÷ የት አካባቢ ምን ዓይነት አፈር አእንዳለ፣ የትኛው አካባቢ አሲዳማ እንደሆነ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንደሚሰጥና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለመወሰን እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡
ባለሙያዋ አክለውም ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጅዎችን ለመቅረጽ እና ለየትኛው አፈር ምን ዓይነት ማዳበሪያ ያስፈልጋል ሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶችን አጠባበቅ እና መልሶ ማቋቋሚያ ስልቶችን ለማዘጋጀት ወሳኝ ነው ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.