Fana: At a Speed of Life!

በከተማ ግብርና ልማት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ምክክር መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትኩረቱን በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገና ሌሎች የክልል ከተሞችን የግብርና እንቅስቃሴ የዳሰሰ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
ምክክሩ÷ በግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በግብርና ሚኒስቴር ተዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው የተካሄደው፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ እንደገለጹት÷ የከተማ ግብርና ስራ እንደ ሀገር የተያዘውን ልማት ለማሳካት፣ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ትልቅ ሚና አለው፡፡
የምምክሩ ዓላማም÷ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማ ግብርና ያሉ ምቹ ሁኔታዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየትና እንዲፈቱ በማድረግ እንዲሁም የዘርፉ ባለሃብቶች ተሳትፏቸውን በማሳደግ ሌሎችም ተሞክሮ እንዲያገኙበት ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ የከተማ ግብርና እንስሳት ዘርፍ አጠቃላይ ሁኔታ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና ልማቱ ላይ ያለው ሁኔታ የሚዳስሱ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ÷ እያደገ ለመጣው የሕዝብ ቁጥርና የከተሜነት መስፋፋት የከተማ ግብርና ድርሻ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የከተማ ግብርና በትንሽ ቦታ የሚተገበር አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ገቢ የሚያሻሻልና የምግብ ዋስትናን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸው÷ ዘርፉን በተቀናጀ መንገድ እያለሙ ያሉ ዜጎችም ተጠቃሚ ሆነዋል ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆልቲ ካልቸር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን÷ በአዲስ አበባ ከተማ እየተተገበረ ያለው የከተማ ግብርና ለሌሎች ከተሞችም አስተማሪ የሚሆን ተሞክሮ የታየበት ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽነር አቶ ባዩ ሽጉጤ እንደገለፁት÷ ግብርናው እስካሁን ገጠርን ማዕከል ያደረገ ቢሆንም አሁን ግን ከተማውንም ማዕከል በማድረግ እራሱን እንዲችል መደረጉ ትልቅ እምርታ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የከተማ ግብርና ግንዛቤው በሁሉም ባለድርሻ አካላት እድገት አሳይቷ ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.