Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ “እንችላለን” ብለን የተነሳነውን እውን ለማድረግ እየሰራን ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብን ተሳትፎ በማረጋገጥ የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ “እንችላለን” ብለን የተነሳነውን እውን ለማድረግ እየሰራን ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ተናገሩ፡፡
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 2ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በፓናል ውይይቱ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የሲዳማ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፣ የሲዳማ ክልል ምክርቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋንታዬ ከበደ፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ወጣቶች ተገኝተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባደረጉት ንግግር÷ ሲዳማ ክልል ከሆነ ወዲህ የመጡ ለውጦች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው በሁለት ዓመት ውስጥ የመጣው ለውጥ በዓይን የሚታይ ነው ብለዋል።
በክልሉ የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁሉንም ጥያቄ በአንድ ጀንበር ለመመለስ ባይቻልም በሁለት ዓመት ውስጥ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ ደስታ÷ ለአብነትም በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በድልድይ ሥራ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ በከተማ ልማት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በቱሪዝምና በመሳሰሉት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
በሁለት ዓመት ውስጥ ይሄን ያህል ከሰራን በቀጣይ ዓመታት ሲዳማን በብልጽግና ማማ ላይ አድርሰን በድል እናሻግራለን ብለዋል።
ተሳታፊዎቹ በክልሉ ውስጥ የተሰሩ የልማት ስራዎችን በትናንትናው ዕለት ተዘዋውረው መመልከታቸውን የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ተሳታፊዎችም በክልሉ በሁለት ዓመት የተሰሩ ስራዎች የሚያኮሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.