Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የ26 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ያልተማከለ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማጠናከሪያ መርሃ ግብር የሚውል የ26 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ።

መርሃ ግብሩ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል።

የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፥ መርሃ ግብሩ ክልሎች ባልተማከለ አስተዳደር የአደጋ ስጋትን በራሳቸው እንዲቀንሱ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

ስለሆነም ከክልሎች ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ይረዳል ነው ያሉት።

በአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሚደርሰውን ችግር ቀድሞ ለመከላከል መንግስት ፖሊሲ ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ዮሐን ቦርግስታም በበኩላቸው፥ አደጋ በማንኛውም ጊዜ ሊደርስ የሚችል በመሆኑ ቀድሞ መዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ባልተማከለ አስተዳደር የአደጋ ስጋትን ለመከላከል ለምታደርገው እንቅስቃሴ ኅብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.