Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክልል ደረጃ 4ኛውን የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተካላ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኢሉ አባቦር ዞን ያዮ ወረዳ በክልል ደረጃ አራተኛውን የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተካላ አስጀመሩ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ የያዮ ደን የኦሮሞ ሕዝብ የተፈጥሮ ሃብቶችን በተለይም የደን እንክብካቤ ላይ ያለውን ባህላዊ እሴት በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መረሐ ግብር የተሠራውን ሥራ አጠናክሮ በማስቀጠል የክልሉን የደን ሽፋን ለማሳደግ በትጋት መሥራት ይገባል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።
በዚህ ዓመት በክልሉ እስካሁን 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን የገለጹት አቶ ሽመልስ፥ የተዘጋጀውን 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል መረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ ባለፉት ሦስት ዓመታት 9 ቢሊየን ችግኝ መተከሉን እና ከ7 ቢሊየን በላይ መፅደቁን ገልፀዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻው የአርሶ አደሩን ምርት እና ምርታማነት በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት።
ባለፈው ዓመት ከታየው ውስንነት በመማር ዘንድሮ 4 ነጥብ 8 ቢሊየን የተለያየ ጥቅም ያላቸው ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
የኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ተናግረዋል።
በግብርና ዘርፍ የተያዘውን የተጠናከረ የልማት ጅማሮ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ኦቢኤን ዘግቧል፡፡
በዞኑ ያለውን የያዮ ደን በማልማት ከካርቦን ሽያጭ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እና የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.