Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚ በይፋ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ከዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ባገኘው ድጋፍ የአዕምሯዊ ንብረት ግንዛቤን ለማሳደግ የላቀ ድርሻ እንዳለው የታመነበትን የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚ በይፋ ከፈተ፡፡
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን በማስከፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት÷ አዕምሯዊ ንብረት ቀጣይነት ያለው እና ሰፊ ልማትን በማበረታታት ፈጠራን እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስተዋወቅ ወሳኝ ነው፡፡
የሀገራዊ የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚ ምስረታ በብዙ ደረጃዎች እና በባህሪው አዕምሯዊ ንብረትን የልማት መሳሪያ ለማድረግ ለሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ የአዕምሯዊ ንብረት አካዳሚ መመስረት የማንኛውም ሀገር የእድገት ደረጃ እና የፈጠራ አቅምን የሚያሳድግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አካዳሚውን ለማቋቋም ከተከናወኑ ተግባራት ዋና ዋናዎቹ÷ የቢዝነስ ዕቅድ ማዘጋጀት፣ ሰልጣኞች መመልመል፣ የትምህርት ስርዓት መቅረጽ እና የማሰልጠኛ ሞጅሎችን ሀገራዊ የማድረግና የመተርጎም ስራዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በአሰልጣኞች ስልጠናው ላይ ከከፍተኛ ትምህርት፣ ከምርምርና ስርጸት ተቋማት፣ ከጋራ አስተዳደር ማህበራት፣ ከፈጠራ ባለሙያዎች እና ከአዕምሯዊ ንብረት ወኪሎች የተውጣጡ ሰልጣኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ መገለጹን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.