Fana: At a Speed of Life!

በማደያዎች የሚታዩ ሰልፎችን ለማስቀረት በቀን ከ10 ሚሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ እየገባ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ነዳጅ ለመቅዳት በማደያዎች የሚታዩ ረጃጅም ሰልፎችን ለማስቀረት በቀን ከ10 ሚሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን የነዳጅ እና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

በአቅርቦት በኩል ክፍተት እንዳይኖርም ቀድሞ በቀን ይቀርብ ከነበረው 9 ሚሊየን ሊትር ወደ 10 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ማሳደጉን የባለስልጣኑ የነዳጅ ስታንዳርድ ጥራት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ ተናግረዋል።

ነዳጅ የጫኑ ቦቴ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ መዘግየት እንዳይፈጠር እና ስርጭቱ ላይ ችግር እንዳይኖር ለማድረግ ኮሚቴ ተዋቅሮ በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት እንደ ሀገር 200 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ከጂቡቲ ተነስተው 18ቱ ሞጆ ወደብ መድረሳቸውን እና የተቀሩት ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰዳባቸው አቶ ለሜሳ ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 8 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች የተቀመጠላቸውን ቀነ ገደብ ባለማክበራቸው ምክንያት ነዳጁን መውረሱን እንዲሁም ሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን አንስተዋል።

የችግሩን መጠን በፍጥነት ለመቀነስ እንዲያስችል እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው÷ በተደረገው ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር በትናንትናው ዕለት 39 ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች አዲስ አበባ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

ነዳጅ ከመነሻው እስከ መዳረሻው ያለውን የክትትል እና ቁጥጥር ሂደት በሰው ኃይል ይደረግ የነበረውን በመሳሪያ በተደገፈ ቴክኖሎጂ ለማድረግ የሙከራ ትግበራ ላይ እንደሆኑ መግለጻቸውንም ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.