Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ክፍያን ለመፈጸም በባለድርሻ ተቋማት መካከል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሔራዊ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ክፍያን ለመፈጸም በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር፣ በኢትዮቴሌኮምና በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መካከል የለማውን መተግበሪያ ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም የመግባቢያ ሰነዱን ተፈራርመዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ በስምምነት ፊርማው ወቅት እንደገለጹት÷ የበለጸገው የክፍያ መተግበሪያ ስራን የሚያቀል ነው፡፡

ያልተመዘገቡ ማደያዎችና የተሽከርካሪ ባለሃብቶችም እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በአገልግሎቱ ለሚፈጠረው ችግር እገዛ ለማግኘት በነጻ የስልክ መስመር 9719 በመደወል ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው የበለጸገው የክፍያ መተግበሪያ በራስ አቅም የለማ መሆኑን ጠቁመው፥ ገንዘብንና ጊዜን የሚቆጥብ ዘመኑን የመጠነ ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።

አቶ አብዱልበር ሸምሱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን ወክለው እንደተናገሩት÷ በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ የተመዘገቡ 164 ሺህ 345 ተሽከርካሪዎች ተለይተዋል።

የድጎማ አፈጻጸሙን ለመተግበር አምስት ደረጃዎች የታዩ ሲሆን÷ የተሽከርካሪዎች አይነት፣ የሚጓዙት ኪሎሜትር፣ የመንገድ ሁኔታ፣ የነዳጅ አይነት ግምት ውስጥ የገቡ ናቸው ተብሏል፡፡
ከተመዘገቡት ተሽከርካሪዎች 140 ሺህ 208 የሚሆኑት በቴሌ ብር መመዝገባቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

ለታለመለት ድጎማ የተመረጡ ተሽከርካሪዎች ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ የከተማ አውቶብሶች፣ ሚኒባሶች፣ ታክሲዎች፣ አገር አቋራጭ አውቶብሶች፣ ለመንግስት ሰራተኞች አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶች መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

መተግበሪያው ለቁጥጥር የሚመች ሆኖ መልማቱ እና በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሚመራ ነውም ተብሏል።

በአገሪቱ አገልግሎት ከሚሰጡ ማደያዎች ውስጥ 860 የሚሆኑት ማደያዎች እስካሁን ድረስ ተመዝግበው አገልግሎቱን ለመስጠት አስፈላጊውን ስልጠና መውሰዳቸውም ተገልጿል፡፡

ድጎማው ለማህበረሰቡ እንጂ ለተሽከርካሪ ባለሃብቶች አለመሆኑን ህብረተሰቡ ሊገነዘብ እንደሚገባም ነው የተገለጸው፡፡

በቴሌ ብር እንዴት መፈጸም እንደሚቻል ኢትዮ ቴሌኮምን ወክለው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ቸርነት የሻምበል÷ ክፍያውን በቴሌ ብር ደህንነቱ በተጠበቀና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ለመፈጸም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.