Fana: At a Speed of Life!

የሀገር ውስጥ ነጻ የንግድ ቀጠና መጀመር የሎጅስቲክስ ዘርፉን ያነቃቃል- ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ውስጥ ነጻ የንግድ ቀጠና መጀመር የሎጅስቲክስ ዘርፉን ያነቃቃል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ተናገሩ፡፡
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ነጻ የንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ ለማስጀመር ያለመ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው፡፡
የሀገር ውስጥ ነጻ የንግድ ቀጠናው በድሬ ዳዋ በሙከራ ደረጃ እንደሚጀመርም በውይይቱ ተገልጿል፡፡
በምክክሩ ላይ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ባደረጉት ንግግር÷ ነጻ የንግድ ቀጠናው እንዲጀመር የተያዘው ዕቅድ የሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠና መመስረት ሀገራዊ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አንድ አካል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
አሁንም ድረስ ያሉ የሎጅስቲክ ክፍተቶች በምርት ጥራት እና ዋጋ ንረት ላይ ተጽዕኖ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
መሰል ችግሮችን ለመቅረፍም ነጻ የንግድ ቀጠና ምስረታው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ ምጣኔ ሀብቱንም ለመደገፍ ያግዛል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር የኋላሸት ጀመረ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ ዕቅዱን ለማሳካት የሎጅስቲክስ ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ነጻ የንግድ ቀጠና በኢትዮጵያ እንዲጀመር ከስምምነት ላይ መደረሱንም ነው የጠቆሙት፡፡

 

ለተጨማሪ መረጃ ቪዲዮውን ይመልከቱ –

በአወል አበራ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.