Fana: At a Speed of Life!

ከቡና ልማት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትጋት መሥራት ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከቡና ልማት የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ተናገሩ፡፡
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳን ጨምሮ የክልል፣ የዞን እና ልዩ ወረዳ አመራሮች በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ የቡና ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካሂደዋል።
አቶ ርስቱ ይርዳ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የጌዴኦ ዞን በኢትዮጵያ ደረጃ በቡና ምርቱና በጥምር ግብርናው እንደሚታወቅ ጠቁመው÷ የዞኑ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮችን ህይወት ለመቀየር በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
ቡናን በጥራት ለገበያ ለማቅረብ የተያዘው ዕቅድ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው÷ በአረንጓዴ ዐሻራ ከሚተከለው 1 ቢሊየን ችግኝ መካከል 80 ሚሊየን ያህሉ የቡና ችግኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክልሉ ዘንድሮ ካለፈው ዓመት የተሻለ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረቡን ገልጸው÷ የቡና ዋጋም የተሻለ መሆኑ አምራቹን ያበረታታል ብለዋል።
ከአርሶ አደሩ ጋር ውለው በማደር ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ እየሰሩ ለሚገኙ የልማት ባለሙያዎች፣ የዞኑ አርሶ አደሮች÷ በቡና፣ በዛፍ ልማት እና በጥምር ግብርና እያደረጉት ለሚገኘው ጥረት አመስግነው የአርሶ አደሮቹ ህይወት እንዲቀየር የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ በንግግራቸው÷ ሰላምን በመጠበቅ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት÷ በየደረጃው እየተሠሩ በሚገኙ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡
በጌዴኦ ዞን በ70 ሺህ ሄክታር ላይ ቡና እየለማ መሆኑንም የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.