Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መሰጠት ተጀምሯል፡፡
በአማራ ክልል ከ359 ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና መስጠት መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ካሴ አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ዛሬ መሰጠት የጀመረው በ5 ሺህ 395 ትምህርት ቤቶች ነው።
ፈተናውም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ከተፈታኞቹ መካከልም ከ193 ሺህ የሚበልጡት ወይም 53 ነጥብ 8 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ፥ ከ19 ሺህ በላይ ፈታኝ መምህራንና የፈተና ተቆጣጣሪዎች መሰማራታቸውን ጠቁመዋል።
ፈተናው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅም በቂ የፀጥታ አካላት በየትምህርት ቤቱ መመደባቸውን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ ሲሆን ፥ የሲዳማክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮው ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ በለኩ ከተማ ሞሮቾ ሾንዶሎ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት የፈተናውን መጀመር መመልከታቸው ተገልጿል፡፡
በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ ፈተና በሁሉም ጣቢያዎች መሰጠት መጀመሩን አቶ በየነ በዚሁ ጊዜ አረጋግጠዋል፡፡
ፈተናው በክልሉ በሚገኙ 774 ትምህርት ቤቶች መሰጠት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
በአንድ ክፍል 25 ተማሪ እንዲቀመጥ ታሳቢ በማድረግ ከ33 ሺህ በላይ ፈታኝ መምህራን መሰማራታቸውንም አቶ በየነ ተናግረዋል ፡፡
የ8ኛ ክፍል ፈተና በሶማሌ ክልል በሚገኙ 731 ትምህርት ቤቶች መስጠት የተጀመረ ሲሆን ፥ 45ሺህ 931 ተማሪዎች እንደሚፈተኑና 226 ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እየፈተኑ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱላሂ አብዲ ፥ ፈተናው የትምህርት ጥራት ከማረጋገጥ አኳያ የመጀመሪያው እርምጃ መሆኑን ገልፀው÷ ለፈተናው ሰፊ ዝግጅት ተደርጎበታል ብለዋል።
በተመሳሳይ ÷በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሰጠት በተጀመረው የ 8ተኛ ክፍል አስተዳደራዊ ፈተና 7 ሺህ 18 የሚሆኑ ተማሪዎች እየተፈተኑ ሲሆን ይህም በገጠር 46 በከተማ ደግሞ 22 ማእከላት በአጠቃላይ 68 ማእከላት ላይ ፈተናው እየተሰጠ እንደሚገኝም የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.