Fana: At a Speed of Life!

ተጨማሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዳይከሰት በተጋላጭ መንደሮች የሚሊሻና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በወገኖቻችን ላይ ተጨማሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዳይከሰት ሁሉንም ተጋላጭ ቀበሌዎች እና መንደሮችን በመለየት አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ነዋሪው ራሱን በተደራጀ መልኩ እንዲከላከል የሚሊሻና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደረግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።

አቶ ደመቀ መኮንን በቄሌም ወለጋ ለተጨፈጨፉ ንጹሃን ዜጎች የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል።

አቶ ደመቀ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በወለጋ አካባቢ አሁንም አሸባሪው የሸኔ ቡድን በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ አሳዛኝ ጭፍጨፋ አካሂዷል ያሉ ሲሆን፥ ጥቃቱ የአማራ ብሄር ተወላጆችን ዒላማ ያደረገና ተጠቂዎችን ለመከላከል ሙከራ ባደረጉ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጭምር ያነጣጠረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ ቡድን ህፃናትን፣ እናቶችን እና ደካማ አረጋውያንን ለይቶ ተደጋጋሚ ጥፋት በመፈፀም ሃገር የማፍረስ ግልፅ ተልዕኮ ያነገበ የተስፋ ቢሶች ጥርቅም መሆኑን በተግባር ማረጋገጡንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ደመቀ እንዳሉት ፥ መንግስት በመላው ሃገሪቱ በተለይም ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈፀምባቸው አካባቢዎች ህግ ለማስከበር፣ ሰላም እና ፀጥታ ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ ለማስቻል ጠንካራ ርብርብ እያደረገ ቢሆንም፤ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች አሸባሪ ቡድኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥፋት መፈፀሙን ቀጥሏል።

በማንኛውም መመዘኛ ድርጊቱ በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ቅንብር እየተፈፀመ ያለ ኢ-ሰብዓዊ እና ዘግናኝ በመሆኑ፤ መንግስት ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር የጀመረውን ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የገለጹት፡፡።

በወገኖቻችን ላይ ተጨማሪ ጥቃትና ጭፍጨፋ እንዳይከሰትም በሁሉም አካባቢዎች ተጋላጭ ቀበሌዎች እና መንደሮችን በመለየት አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንዲሁም ነዋሪው ራሱን በተደራጀ መልኩ እንዲከላከል የሚሊሻና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚደረግም አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ህብረታዊ የትግል እንቅስቃሴያችን እንዲከሽፍ ጠላት አስልቶ በርቀት የሚጠባበቀው የሴራ ውጤት በመሆኑ፤ በተደጋጋሚ በደረሰብን ጥፋት ሳንበረከክ አንድነታችንን አጥብቀን በፅናት እንድንጓዝ አደራ እያልኩ በተጎጂ ወገኖች የተሰማኝን ልባዊ ሀዘን እገልፃለሁ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.