Fana: At a Speed of Life!

አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ “በብዙ ውጣ-ውረድ ውስጥ ሆነን ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል” አሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በብዙ ውጣ-ውረድ ውስጥ ሆነንም ቢሆን ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ የምክር ቤቱን የአፈጻጸም ደረጃ አመላከቱ፡፡

የምክር ቤቱ አማካሪ እና አስተባባሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም የመንግስት ዋና እና ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዎች በተገኙበት፣ የአሥራ አንዱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ተገምግሟል፡፡

አፈ ጉባዔ አቶ ታገሠ በዚሁ ወቅት ፥ ከመንግስት ምስረታው ጊዜ ጀምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ ምክር ቤቱ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡

እንደ ሀገርና እንደ ተቋም የተሠሩ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑ እና በቋሚ ኮሚቴዎች የቀረቡት ተጨማሪ ሀሳቦች አስተማሪ እንደሚሆኑ ነው ያመለከቱት።

ስለሆነም ቆም ብለን በማሰብ፣ ሀገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ የሁላችንም ቀና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ፥ ጥሩ የሠሩ ተቋማት የሚበረታቱበት፣ ያልሠሩት ደግሞ የሚጠየቁበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዲሁ በምክር ቤቱ መሻሻሎች እንዳሉ አንስተው ፥ የምክር ቤቱ አባላት ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የክትትልና ቁጥጥር ሥራቸውን ምክር ቤቱን በሚመጥን ደረጃ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት፡፡

የቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች እና አባላት በሕዝቦች ዘንድ በሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ በሙስና፣ በብልሹ አሠራሮች ላይ ግልጸኝነትን እና ተጠያዊነትን እያረጋገጡ መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ምሕረቱ ሻንቆ በበኩላቸው፥ የምክር ቤቱ ዋና ተግባር በሕገ-መንግስቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት መወጣት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአሥራ አንዱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች በክትትል እና ቁጥጥር፣ በሕግ አወጣጥ፣ በፓርላማ ዲፕሎማሲ እና በሕዝብ ውክልና ሥራዎች ምክር ቤቱ በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

በመሠረተ ልማቶች፣ በሕንጻ ግንባታዎች፣ በዜጎች ፍትሐዊ የቤት ተጠቃሚነት፣ በትራንስፖርት፤ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች፤ እያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ በሚከታተላቸው ተቋማት በውጤት የተመሠረቱ ሥራዎችን በመሥራት፤ የሕዝብን ጥያቄዎች መመለስ እንዳለበትም የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባላት ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.