Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የጎርፍ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖች አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የጎርፍ አደጋ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ከወዲሁ አደጋ እንዳይፈጠር ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሰሞኑን የባሮ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ1 ሺህ 600 ሄክታር በላይ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱ ተመላክቷል።
በጋምቤላ ክልል የክረምት ወቅት ሲመጣ ስጋት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጎርፍ አደጋ መከሰት መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን እንደገለጹት÷ በክልሉ በኑዌር ዞን የሚገኙ አምስት ወረዳዎችና በአኙዋክ ዞን የጆር ወረዳ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ናቸው፡፡
እነዚህ በወንዞችና ተዳፋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ቦታዎች በመሆናቸው የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ለጎርፍ ስጋት ተጋላጭ ለሆነው ማህበረሰብ የቅድመ ጥንቃቄና በክልሉ በስፋት በሚነገሩ ቋንቋዎች አማካኝነት ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የጎርፍ አደጋ በላሬና በመኮይ ወረዳ በ1 ሺህ 650 ሄክታር በሰብል ማሳ ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው÷ አርሶ አደሩ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችንና ውሃን ከማሳ ውስጥ የመቀነስ ሥራዎችን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሰብል የወደመባቸው አርሶ እና ከፊል አርብቶ አደሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የሰብል አይነቶችን እና የጓሮ አትክልቶችን ማልማት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ጋትቤል ተናግረዋል።
በክልሉ ለጎርፍ ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ ቦታዎች መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ዕቅድ በማውጣት ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸው÷ ህብረተሰቡም በክረምቱ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለየ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.