Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የወጣቶች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቢሾፍቱ ከተማ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ በበጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሻገር በጎነትን ተላብሶ በጋራ ከመቆምና በአንድነት ከመትጋት ውጪ ሌላ ምድራዊ አማራጭም ሆነ አቋራጭ መንገድ የለም ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር በየዘርፉ በተለያዩ አካላት እጅግ የሚያስመሰግኑ በርካታ በጎ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው÷ ዘርፉ የሚመራበት ሕግ ለማበጀትና ስርዓት አድርጎ ለማስቀጠል የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ ለማሻገር በአስተዳደር ወሰን ሳንታጠር፣ በፍቅር ተደምረን፣ በጎነትን ተላብሰን፣ በባለቤትነት እና በኃላፊነት ስሜት በትጋት መስራት ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለራሳችን፣ ለማህበረሰባችን እና ለሀገራችን ሁለንተናዊ ለውጥ መሰረት የሆነው በጎነት÷ የሁላችንም መርህ ሊሆን እና ከቃል ባለፈም በተግባር ልናሳይ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው÷ ከሌላው አካባቢ በተለየ በኦሮሚያ ክልል በበጎ ፈቃድ ከሚሰጡ አገልግሎቶች ባሻገር ሁሉም የዜግነት ድርሻውን መወጣት የሚችልበት አዋጅ ፀድቆ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እየተተገበረና ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ላይ÷ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሙና አህመድን ጨምሮ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለማየሁ አሰፋ፣ ክልል አመራሮች፣ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.