Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ ፓርላማ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል ድምፀ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ፓርላማ ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ዘመቻ እንዲቀጥልና ለሠራዊቱ አስፈላጊው ሕዝባዊ ድጋፍ እንዲደረግለት የሚፈቅዱ ሁለት ረቂቅ ሕጎችን ለማጽደቅ የመጀመሪያ ዙር ድምፀ ውሳኔ ሰጠ።

ረቂቅ ሕጎቹ ወታደራዊ ዘመቻውን ለመደገፍ ማናቸውም ተቋማት በተለያዩ ቁሳቁሶችና በስው ኃይል ሠራዊቱን ለማጠናከር ያለሙ መሆናቸው ተገልጿል።

እርምጃዎቹ የአገሪቱ ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያቀርቡና ሰራተኞቻቸውም የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዲሰሩ ጭምር የሚያስገድዱ እና ሩሲያን በጦርነት የኢኮኖሚ መሠረት ላይ እንድትቆም የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።

ሩስያ በዩክሬን እያካሄደች ያለችው ወታደራዊ ዘመቻ ከተጀመረ 19 ሳምንታትን አስቆጥሯል።

በፈረንጆቹ የካቲት 24 በዩክሬን ወታራዊ ዘመቻ የጀመረችው ሩስያ፥ ዋና ከተማዋን ኪየቭን ለመያዝ ያደረገችው የመጀመሪያ ሙከራ ያልጠበቀችው ኪሳራ ያደረሰባት በመሆኑ የውጊያ አቅጣጫዋን በመቀየር፥ በሀገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛቶች ላይ በማተኮር ዘመቻዋን እያሰፋችና በዩክሬን ላይ ከባድ ኪሳራ እያደረሰች መሆኗንም ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የሀገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሪ ቦሪሶቭ በመከላከያ ኢንዱስትሪ ላይ ያለው ሸክም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ያሉ ሲሆን፥ የጦር መሣሪያ እና ጥይት አቅርቦትን ለማረጋገጥ የወታደራዊ-ኢንዱስትሪ ተቋማትንና እና በሥራቸው ያሉ ኢንተርፕራይዞችን ሥራ ማጠናከር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ተንታኞች እንደሚሉት የዩክሬን ደጋፊና የጦር መሣሪያ አጋፋሪ የሆኑት ምዕራባውያን አገሮች በሩስያ ላይ በተከታታይ የማዕቀብ ማዕበል ያወረዱባት ሲሆን፣ ለዩክሬን የሚሰጡትን የጦር መሣሪያ አቅርቦት፣ የገንዘብ ድጋፍ አና በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙትን የኔቶ ኃይላቸውን አጠናክረዋል። “ሞስኮ ጉዳዩን በሩሲያ ላይ የሚካሄድ ‘የውክልና ጦርነት’ አካል አድርጋ ነው የምትመለከተው” ሲሉም ይገልጹታል።

የሩስያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪሶቭ ለሕግ አውጭው ምክር ቤት (ዱማ) በሰጡት ማብራሪያ፥ “በአሁኑ ጊዜ ምዕራባውያን ሀገሮች ከሩሲያ ጋር በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ ወታደራዊ ኃይላቸውን እና የማዕቀብ ጫናቸውን እያጠናክሩና ለዩክሬን የጦር መሣሪያ አቅርቦት እየጨመሩ ባሉበት ሁኔታ፥ የአሁኑ ውሳኔ አስፈላጊነት ተጋኖ ሊታይ አይገባውም” ነው ያሉት፡፡

ለዱማው ከቀረቡት ሁለት ረቂቅ ሕጎች አንዱ በታችኛው የፓርላማ ምክር ቤት በንባብ ቀርቦ ይሁንታ ያገኘ መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ሀገር በወታደራዊ ተልዕኮዎች ወቅት ልዩ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን ልትጥል ትችላለች” በሚለው ጉዳይ ላይ ከውሳኔ መደረሱን ገልፀዋል፡፡

ይህም ተቋማት ቁሳቁሶችን እና አገልግሎቶችን ለውትድርና አገልግሎት እንዲያቀርቡ ይጠይቃል ነው ያሉት።

ሁለተኛው ረቂቅ ሕግ ደግሞ መንግስት የሥራ ሰዓትን የመቆጣጠር እና ኩባንያዎች ባላቸው የእረፍት ቀናት ላይ የመወሰን መብት እንዲሰጠው የሠራተኛ ሕጉ እንዲሻሻል የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ለውትድርና ዕቃዎችን የሚያቀርቡ የድርጅቶች ሰራተኞችም በምሽት ፣ በሳምንቱ መጨረሻ እና በበዓላት እንዲሁም ያለ ዓመት ፈቃድ እንዲሰሩ ሊገደዱ ይችላሉ ሲሉም ነው የገለፁት።

ይሁን እንጂ በአዲሱ ሕግ ከፍተኛ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ጥቅም ላይ እንደማይውል ጠቁመው ፥ ነገር ግን ሰራተኞች ተጨማሪ ክፍያ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች አሁንም በዱማው ውስጥ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ንባቦችን ማለፍ አለባቸው ያሉት አፈ ጉባኤ ቪቼስላቭ ቮሎዲን፥ በነገው ዕለት ውይይቱ በዝግ እንደሚቀጥል ነው ያስታወቁት።

ከዚያም በላይኛው የፓርላማ ምክር ቤት ተገምግሞ በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊርማ ተፈርሞበት ሕግ ሆኖ ይፀድቃል ሲሉም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.