Fana: At a Speed of Life!

የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ መደረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዋጋ ማሻሻያው ከነገ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ባስተላለፈው የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሰራር እና የመሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም ውሳኔ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል።

ሚኒስቴሩ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ክለሳን አስመልክቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በግንቦት ወር የዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ቤንዚን በሜትሪክ ቶን 1300 ዶላር ፣ ናፍጣ በሜትሪክ ቶን 1162 ዶላር ከነበረበት፥ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ቤንዚን በሜትሪክ ቶን 1364 ደላር፣ ናፍጣ በሜትሪክ ቶን 1322 ዶላር የደረሰ መሆኑን አውስቷል።

መንግስት የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ አልፎ አልፎ ከ10 በመቶ ያልበለጠ ጭማሪ እያደረገ የቆየ በመሆነ ቤንዚን በሊትር 36.87 ብር ፣ ናፍጣ በሊትር 35.43 ብር መሸጫ ዋጋ ሆኖ እንዲቆይ ማድረጉንም አስረድቷል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ በነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በወር በአማካይ ወደ ተጠቃሚው መተላለፍ የነበረበት 10 ቢሊየን ብር ጉድለት ወደ መንግስት እየተመዘገበ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ 146 ቢሊየን 624 ሚሊየን 248 ሺህ 889 ብር ከፍተኛ ዕዳ ለመሸከም መገደዷን ገልጿል፡፡

ስለሆነም መንግሥት የዕዳ ጫናን ደረጃ በደረጃ ለማስቀረት እንዲቻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ እንዲተገበር ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል ተጽዕኖ በማያስከትል ሁኔታ የሕዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን በመለየት የድጎማ ተጠቃሚ ለማድረግ የነዳጅ ዋጋ ክለሳና የታለመ ድጎማ ትግበራ ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ መግባት አስፈልጓል ብሏል፡፡

በመሆነም የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በዓለም ገበያ በተገዛበት መሸጫ ዋጋ መነሻ በማድረግ በቀጥታ ቢሰላ የአዲስ አበባ ከተማ የ1 ሊትር ናፍጣ መሸጫ ዋጋ ብር 91 ከ23 ሳንቲም እና የቤንዚን መሸጫ ዋጋ በሊትር 82 ብር ከ07 ሳንቲም መሸጥ የነበረበት ሲሆን፥ አሁንም ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከዓለም ገበያ መሸጫ ዋጋ የልዩነቱን 75 በመቶ የሚሆነውን ጫና መንግስት በመሸከም፥ ቀሪውን 25 በመቶ ለተጠቃሚው እንዲተላለፍ በመወሰን የነዳጅ ምርቶች ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ መጠነኛ ክለሳ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው ያስታወቀው።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ መሰረት፦
ቤንዚን — 47 ነጥብ 83 በሊትር
ነጭ ናፍጣ — 49 ነጥብ 02 በሊትር
ኬሮሲ — 49 ነጥብ 02 በሊትር
ቀላል ጥቁር ናፍጣ — 53 ነጥብ 10 በሊትር
ከባድ ጥቁር ናፍጣ — 52 ነጥብ 37 በሊትር
የአውሮፕላን ነዳጅ — 98 ነጥብ 83 በሊትር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከላይ የተገለጸው የቤንዚን፣ የኬሮሲንና የነጭ ናፍጣ ዋጋ ላይ ለህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ወይም የታለመ ድጎማ ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች 15 በመቶ በመንግስት እንዲደጎምና ቀሪውን 10 በመቶ እንዲከፍሉ በማድረግ የድጎማ መጠኑን በቴሌ ብር ተመላሽ እንዲሆንላቸው ይደረጋል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

የዋጋ ማስተካከያ የተደረገባቸው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በዝርዝር ከነገው /ሰኔ 29/2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ማደያዎች ሁሉ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቋል።

የነዳጅ ምርቶች ወቅታዊ የዓለም አቀፍ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሸማቹ ህብረተሰብ ምርቶቹን በቁጠባ የመጠቀም ባህሉን እንዲያዳብር እንዲሁም የታለመ የነዳጀ ድጎማ ተጠቃሚዎች የነዳጅ ምርቱን ለታለመለት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ ማዋል የሚኖርባቸው መሆኑን ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

ሁሉም የህብረተብ ክፍል፣ የፀጥታ አካላትና ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.