Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ ሪፎርም ሰራዊቱ ከፓርቲ ታዛዥነት ወጥቶ ህዝባዊና ሀገራዊ ሰራዊት እንዲሆን አድርጓል-ሌ/ል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ሪፎርም ሰራዊቱ ከፓርቲ ታዛዥነት ወጥቶ ህዝባዊና ሀገራዊ አደረጃጀትና አስተሳሰብ እንዲኖረው ማድረጉን በመከላከያ ሰራዊት የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ገለጹ፡፡

በመከላከያ ሰራዊት የ8ኛ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል እንደገለጹት÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በቆየበት የስልጣን ዘመን የኢትዮጵያን አንድነትና የሀገር ሉዓላዊነት ያስቀጥላሉ ያላቸውን ተቋማት በማፍረስ ተጠምዶ ነበር፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን የአንድ አካባቢ ሰዎች በበላይነት እንዲይዙት በማድረግ አንድ አይነት ሀገራዊ አስተሳሰብ ያለው ሰራዊት ከመገንባት ይልቅ ህወሓት እንደ ፓርቲ የሚፈልገውን ጉዳይ ማስፈፀሚያ መሳሪያ አድርጎት ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱን አንድነት በመናድ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀድሞ የሸረበውን ሴራ እውን ለማድረግም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሰራዊቱ ላይ ጥቃት በመክፈት የሀገር ክህደት መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት የሀገራዊ ሰራዊት ቅርጽ የያዘው ከለውጡ በኋላ በተሰራ የሪፎርም ስራ ነው የሚሉት ሌተናል ጀነራል አሰፋ ቸኮል÷ ሰራዊቱ ከብሔር፣ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ አጥር ወጥቶ አንድ አይነት አስተሳሰብ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት በፓርቲ ሰዎች እየተዘወረ የግል ንብረታቸው እስከሚመስል ድረስ ሲቀለድበት እንደነበር አስታውሰው÷ የመከላከያ ሪፎርም ኢትዮጵያን የሚመሰል ሀገራዊ ሰራዊት እንዲኖር አስችሏል ነው ያሉት፡፡

ሪፎርሙ ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸው ተቋማት በሴራ ከፍና ዝቅ ቢሉም ተመልሰው ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠራቸው የማይቀር መሆኑን ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት እራሱን እያደራጀና እያጠናከረ አስተማማኝ ቁመና ላይ መድረሱንም ገልጸዋል ሌተናል ጄኔራል አሰፋ።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.