Fana: At a Speed of Life!

ፓርላማው ዛሬ ባካሄደው 6ኛው ልዩ ስብሰባ በወቅታዊ የፀጥታ እና በንጹሐን ዜጎች ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሐሳብ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች 6ኛው ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛው ልዩ ስብሰባ፤ በወቅታዊ የፀጥታ እና በንጹሐን ዜጎች ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የውሳኔ ሐሳብ አሳለፈ፡፡
 
የዕለቱን መርሐ-ግብር በግፍ ለተጨፈጨፉት ዜጎች የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት በማድረግ የጀመረው ምክር ቤቱ፥ የሚከተሉትን የውሳኔ ሐሳቦች ማሳለፉን አስታውቋል፡፡
 
ፓርላማው በሀገራችን በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
 
በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 50 (3) መሠረት የፌዴራሉ መንግስት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ተጠሪነቱም ለሀገሪቱ ሕዝብ ነው፤ ውክልናቸውም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡
 
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ረዥም ታሪክ ካላቸው አገራት አንዷ ናት፡፡
 
በአፍሪካ ደረጃ በቀኝ ገዥዎች ያልተገዛች ለአፍሪካ አገሮች ነፃነት ግንባር ቀደሙን አስተዋጽዖ ያደረገች፣ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩባት፤ የተለያዩ ኃይማኖቶች እና ባህሎች ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር ናት፡፡
 
ይሁን እንጂ ባለፉት 27 ዓመታት የተዘራው አስከፊ እና ከፋፋይ የዘር ጥላቻ በሕዝብ ውስጥ ዘግናኝ እና አስከፊ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር ከፍቷል፡፡
 
ከዚህም የተነሳ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ በሲቪል ዜጎች ላይ ሊፈጸም ችሏል፡፡
በመሆኑም በአገራችን በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ጭፍጨፋ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአማራ ፣ በአፋር ክልሎች እና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በንጹሐን ዜጎቻችን እንዲሁም ፀጥታና ደህንነት ለማስጠበቅ በተንቀሳቀሱ የፀጥታ አካላት ላይ ለደረሰው ሕይወት መጥፋት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርጊቱን እጅግ በጣም በመኮነን የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኗል::
 
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ቀርቧል፡
 
2/ የሕግ መሠረት
 
ሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (7) መሠረት በሥራ አፈጻጸም ረገድ የሚታዩ መሠረታዊ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶችና የሀገርን ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች ሲከሰቱ አስፈላጊው እርምጃዎች እንዲወሰዱ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
 
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀጽ 16 መሠረት ከመደበኛ የስብሰባ ጊዜ ውጭ ባሉት ቀናት ልዩ ስብሰባ ሊያካሄ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በደንቡ አንቀጽ 64/2/ ለ እና ሐ መሠረት ም/ቤቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሊያስተላልፍ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
 
3/ ውሳኔ
 
በዚህ መሠረት በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ እጅግ በመኮነን የሚከተለው ውሳኔ ተላልፏል
 
ሀ. በግፍ ለተጨፈጨፉ ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲደረግ፣
 
ለ. በአገራችን በየትኛውም ክልልና አካባቢ በሲቪል ዜጎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ያስከተሉ እና ንብረት ያወደሙ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ፣
 
ሐ. በየደረጃው ያለው አመራር አካል የፀጥታ አካል እና የፍትህ ተቋም የሕዝቡን ደህንነትና ሠላም በጥብቅ እንዲያስከብር፤ አጥፊዎች ለሕግ ተጠያቂነት እንዲቀርቡ እንዲደረግ፣
 
መ. ከመንደራቸው እና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በአስቸኳይ እንዲሰራ፣
 
ሠ. የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከየትኛውም ጊዜ በላይ በወንድማማችነት፣ በአብሮነት እና በአንድነት እንዲቆሙ፣
 
ረ. በምክር ቤቱ የበላይ አመራር የሚሰየሙ ስብጥሩ ሁሉንም ብዝሀነቶች ታሳቢ ያደረገ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን በማጣራት ምክር ቤቱ እና ለሕዝቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው ለማስቻል፥ እንዲሁም ለቀጣይ እርምጃዎች የሚረዳ ምክረ-ሀሳብ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.