Fana: At a Speed of Life!

ሰራዊቱ በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ለትውልድ አሻራውን እያኖረ ነው – ሌ/ ጀኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰራዊቱ በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ችግኝ እየተከለ ለትውልድ አሻራውን ያኖራል ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት በቢሾፍቱ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ግቢ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
 
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በዚህ ወቅት ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እየተቀጣች መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁላችንም ለአረንጓዴ ልማት በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ አየር ሃይል በአንድ እጁ የኢትዮጵያን ጠላቶች እየተዋጋ በሌላ እጁ ችግኝ እየተከለ ለትውልድ የሚሻገር አሻራውን እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
 
 
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለአገር ሉአላዊነትና ለህዝቦች ሰላም ማስከበር ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
በተመሳሳይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የሚኒስቴሩን የ2014 የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስጀምረዋል።
 
ዶክተር አብርሃም በላይ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፥ ዛሬ በመከላከያ ሚኒስቴር ደረጃ የተጀመረው የችግኝ ተከላ በቀጣይ በሁሉም ዕዞች እና ክፍሎች ተጠናክሮ ይቀጥላል።
 
ሚኒስትሩ አክለውም ዛሬ የተተከሉት ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ እንደ አፕል፣ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ዘይቱን፣ ቡና እና የመሳሰሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።
 
በመርሐ ግብርሩ ላይ በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት የሚገኙ ጀኔራሎች፣ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች፣ የሰራዊት አባላት እና ሲቪል ሰራተኞች በጎልፍ ክበብ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኞችን መትከላቸው ተገልጿል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.