Fana: At a Speed of Life!

በሐምሌ ወር የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ከፍተኛ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐምሌ ወር የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ከፍተኛ ጎርፍ ስለሚኖር በተዳፋትና ገደላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳስቧል፡፡
የኢንስቲትዩቱ መግለጫ እንዳመላከተው÷ በሐምሌ ወር የመጀመሪያዎች 10 ቀናት በሀገሪቱ መደበኛ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ነጎድጓዳማ እና በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ይጠበቃል። በዚህም በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚኖረው የዝናብ ሁኔታ ከባድ እና ጎርፍ ሊያስከትል ይችላል ብሏል መግለጫው፡፡
በምዕራባዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች አጋማሽ እና መካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከ100 እስከ 200 ሚሊ ሜትር፣ በተወሰኑ ቦታዎች ከ200 ሚሊ ሜትር በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅም አመላክቷል፡፡
በሐምሌ ወር በመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡
በአብዛኛው የዓባይ፣ ባሮ-አኮቦ፣ ተከዜ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞጊቤ፣ አፋር-ዳናከል፣ የላይኛውና መካከለኛው ዋቢ-ሸበሌ እንዲሁም ገናሌ-ዳዋ ተፋሰሶች ከፍተኛ እርጥበት እንደሚኖራቸውም ተመላክቷል፡፡
በታችኛው ገናሌ-ዳዋ፣ ስምጥ ሸለቆ እና ኦሞ-ጊቤ ተፋሰሶችም መጠነኛ እርጥበት ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ሊጋለጡ ስለሚችሉ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኢንስቲቲዩቱ አሳስቧል።
የዝናቡ ሁኔታ በመኸር አብቃይ እና ዘር መዝራት ባልተጀመረባቸው አካባቢዎች የተሻለ እርጥበት ስለሚኖር አርሶ አደሮች አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.