Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያና ሱዳን መሪዎች ያደረጉት ውይይት ችግሮችን በምክክር በመፍታት የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና ሱዳን መሪዎች ያደረጉት ውይይት ችግሮችን በምክክር በመፍታት የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከር ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከ39ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከሱዳን የሽግግር መንግስት ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ጋር በናይሮቢ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

መሪዎቹ በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን÷ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።

የመሪዎቹን ውይይት የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን÷ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ወዳጅነት ማጠናከር እንደሚገባ መሪዎቹ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ የግጭት ምንጭ ይሆናል ብላ እንደማታምን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውንም አመላክተዋል።

በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አሁንም በጠንካራ መስተጋብር በጋራ እየኖሩ መሆኑን ጠቅሰው÷ ከዚህ አኳያ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመልማት መስራት እንጂ ወደ ግጭት መግባት እንደሌለባቸው መሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተው መነጋገራቸውንም ነው የገለጹት።

ከድንበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ተቋማትን ባሳተፈ መልኩ በመፍታት የሁለቱን ሀገራት መተማመን ማጠናከር እንደሚገባም  መገለጹን ጠቁመዋል፡፡

ይህንን ስራ ሊያሳልጥ የሚችል ኮሚቴ መቋቋም እንዳለበትም መሪዎቹ መነጋገራቸውን አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የህዳሴ ግድብን በሚመለከትም በአፍሪካ ህብረት የተያዙ ጥረቶች ተጠናክረው በሚቀጥልበት ጉዳይ ላይ ሁለቱ መሪዎች ምክክር ማድረጋቸውን ጠቅሰው÷ ግድቡ የቀጠናው የልማትና ትስስር ምንጭ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.