Fana: At a Speed of Life!

አብን በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀሙ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎችን የሚመረምር ልዩ አቃቤ ህግ በአዋጅ እንዲቋቋም እና የወንጀል ፈፃሚዎች በግልፅ ችሎት እንዲዳኙ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ  የተፈፀሙ አሰቃቂ  ጭፍጨፋዎችን የሚመረምር ልዩ አቃቤ ህግ በአዋጅ እንዲቋቋም እና የወንጀል ፈፃሚዎች በግልፅ ችሎት እንዲዳኙ ጠየቀ፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የፓርቲው ሊቀ መንበር  ዶክተር በለጠ ሞላ፥ ባለፉት ዓመታት በተሰራው የተሳሳተ ትርክት በህዝቦች ላይ የተቀናጀ  ጭፍጨፍ ሲካሄድ መቆየቱን አብራርተዋል፡፡

“ላለፉት አራት ዓመታትም የወንጀል አራማጁ እና ሽብርተኛው የሸኔ ሠራዊት ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን የንፁሃን ግድያ ያለ ተከላካይ አጠናክሮ ቀጥሏል” ሲሉ አንስተዋል።

በብዙ ምዕራፍ በተከፈለው  የዚህ የተቀናጀ ፣ ተከታታይ እና ስልታዊ የንጹሃን ግድያም ብዙዎች ውድ  ህይወታቸውን እንዲሁም ሃብትና ንብረታቸውን አጥተዋል ነው ያሉት።

የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በተመለከተም  አብን በወለጋ እና አካባቢው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ እና በፌደራል የፀጥታ ተቋማት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ እንዲሁም  የጥቃቱ ሰለባ እና ተጋላጭ ዜጎች ራሳቸውን ለመከላከል ይረዳቸው ዘንድ በሚሊሻነት እንዲደራጁ  ጠይቋል ፡፡

በክልሉ ማንነት ተኮር  ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ቅስቀሳ ሲያደርጉ እና  እያደረጉ ያሉ  አካላት መኖራቸውን የጠቆመውፓርቲው ÷ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ወንጀሉ ተገቢው እውቅና እንዲያገኝ ይረዳ ዘንድ ብሄራዊ የሀዘንቀን እንዲታወጅ ሲል አመልክቷል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.