Fana: At a Speed of Life!

በዝናብ እጥረት ምክንያት ከ190 ሺህ በላይ ህዝብ በኮንሶ ለምግብ እጥረት ተጋላጭ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮንሶ ዞን በዝናብ እጥረት ከ190 ሺህ በላይ ህዝብ ለምግብ እጥረት ተጋላጭ እንደሆኑ የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ጽኅፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በበልግ ወቅት የዘነበው የዝናብ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ አጥጋቢ የእርሻ ምርት አለመሰብሰቡንም ጽኅፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ወቅቱን ባልጠበቀ እና በተዛባ የዝናብ መጠን ምክንያት ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር የተሸፈነ መሬት ምርት መጥፋቱን የጽኅፈት ቤቱ ባለሙያ አቶ ዘርፉ ላቀው አስታውቀዋል፡፡

በበልግ ወቅት የሚጠበቀው የዝናብ መጠን መቀነስ የፈጠረው ችግር የምርት መቀነስ ብቻ ሳይሆን የተፋሰስ ወንዞች እንዲቀንሱና ለእንስሳት መኖ ይሆኑ ዘንድ የተከለሉ የግጦሽ መሬቶችም እንዲደርቁ እና እንስሳቱ ለምግብ እጥረት እንዲዳረጉ ማድረጉንም ነው አቶ ዘርፉ ያስረዱት፡፡

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በዞኑ በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚረዱትን ተጠቃሚዎች ሳይጨምር በድርቅና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ከ126 ሺህ 800 በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፌዴራልና የክልል መንግስትን የምግብ ግብዓት ድጋፍ እንደሚፈልጉም ነው የተጠቆመው፡፡

ከዚህ ቀደም መንግስት ሕጻናትን ጨምሮ በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ቢያደርግም በቂ አለመሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በበልግ በቂ ዝናብ ባለመገኘቱ የጤፍ፣ በቆሎ፣ማሽላ፣ ቦሎቄ፣ ማሾ፣ ሰሊጥና ሱፍ በድምሩ 30 ሺህ 565 ሄክታር ላይ የተዘራ ሰብል መውደሙን የኮንሶ ዞን ግብርና መምሪያ የአደጋ ስጋትና ቅድመ-ማስጠንቀቂያ ጽኅፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ እንደሚከሰት መጠቆሙን የኮንሶ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.