Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4ኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 30፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በክልሉ 4ኛውን ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ክልል አቀፉ መርሐ ግብሩ “አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል በአሶሳ ዞን ዑራ ወረዳ አምባ 5 ቀበሌ ነው የተካሄደው፡፡
በመርሐ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳ አመራሮችና የቀበሌው ማኅበረሰብ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፣ በክልሉ በ4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ45 ሚሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ችግኞችን መትከል ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ሠላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ችግኞችን ለመትከል መረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ አሻድሊ፣ በዘንዶሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር በግል 100 ችግኞችን ለመትከል ማቀዳቸውን ገልጸው፣ አመራሩ በላቀ ሁኔታ እንዲሳተፍም ጠይቀዋል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች ፍሬ መስጠት ጀምረዋል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ የመጽደቅ ምጣኔውም በአማካይ ከ84 በመቶ በላይ ነው መሆኑን ገልጸዋል።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በመንከባከቡ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ርዕሰ-መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በክላስተር መትከል ፋይዳው የላቀ በመሆኑ፣ ዘንድሮ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.