Fana: At a Speed of Life!

“ችግኝ ተክለን እየተንከባከብን፥ የሃይማኖትና የብሔር አክራሪነትን እንነቅላለን” – የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰው ልጆች እስትንፋስ መሠረት የሆኑ እፅዋቶችን ተክለን እየተንከባከብን የሰው ልጆች ክፉ ነቀርሳ የሆኑ የሃይማኖት አክራሪነት እና ጽንፈኛ ብሔርተኝነትን ነቅለን ለማስወገድ እንሰራን ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፣ የክልሉ አመራሮች እና የፀጥታ አካላት በሐረሪ ፖሊስ ማሰልጠኛ ችግኝ ተክለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሰው ልጆች እስትንፋስ መሠረት የሆኑ እፅዋቶችን ተክለን እየተንከባከብን የሰው ልጆች ነቀርሳ የሆኑ የሃይማኖት አክራሪነት እና ብሔርተኝነትን ከክልሉ ነቅለን ለማስወገድ እንሰራን ብለዋል።
የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅም የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላት በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ከሀሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑን ገልጸው÷ የተተከሉ ችግኞች ፍሬ እንዲያፈሩ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው÷ ባለፉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያን በምስራቅ አፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመረው ስራ ብዙ ውጤቶችን እያስገኘ ነው ብለዋል፡፡
“ዛፎች እንኳ የተለያየ ዘር እና መልክ ይዘው በአንድ ስፍራ በአንድነት ሆነው የየራሳቸውን ፍሬ ለሰው ልጆች መስጠት እየቻሉ፤ የሰው ልጅ በዘር፣ በሃይማኖትና በብሔር ተከፋፍሎ መበላላት የለበትም” ብለዋል።
መልካም መልካሙን እየተከልንና ክፉክፉውን እየነቀልን ኢትዮጵያን ከብልጽግና ማማ ላይ እናደርሳታለን ያሉት ዶክተር ቢቂላ÷ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩን ከኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጥቅም አኳያ በመቃኘት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ÷ የፀጥታ ዘርፉ ከሚሰራው መደበኛ ስራ ባሻገር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.