Fana: At a Speed of Life!

የ2015 የፌዴራል መንግስት በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሆኖ ፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2015 የፌዴራል መንግስት በጀት አፀደቀ፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ያካሄደ ሲሆን፥ በ2015 የፌደራል መንግስት በጀት ላይ በምክር ቤቱ የተገኙ እና ከህዝብ የተሰበሰቡ ግብዓቶችን መሰረት አድርጎ በመወያየት ነው ያፀደቀው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የ2015 የፌደራል መንግስት በጀት፥ ብድር መቀነስ፣ የበጀት ጉድለት መቀነስ፣ ያለን ሀብት በቁጠባ መጠቀም እና የዋጋ ንረትን ማረጋጋት የሚሉ ነጥቦችን የትኩረት አቅጣጫ እንዳደረገ ተናግረዋል።
እንደዚሁም መልሶ ማቋቋም፣ ሰብዓዊ እርዳታ እና የሀገር ደህንነት እና ሰላምን ማስጠበቅን በማጠናከር ላይ ትኩረት እንዳደረገም ተመልክቷል።
የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ዝግጅት በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈጸም አኳያ፣ የሀገር ደህንነትን ከማስጠበቅ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳትና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ ከማቋቋም፣ ቀጣይ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎችን ማሳካት ላይ ማዕከል በማድረግ እንደተዘጋጀ ነው የተጠቀሰው።
በግብርና የጀመርነውን አስደማሚ ስራ ለማስቀጠልን እና ፕሮጀክቶችን በጊዜ ለማጠናቀቅ በጀቱ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አብራርተዋል።
ለ2015 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ ብር 345 ቢሊየን፣ ለካፒታል ወጪ ብር 218 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 209 ነጥብ 38 ቢሊየን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 14 ቢሊየን የተያዘ ሲሆን፥ አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2015 ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሆኖ ፀድቋል፡፡
ከ2014 በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የ111 ነጥብ 94 ቢሊየን ብር ወይም የ16 ነጥብ 59 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው የተባለው፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.