Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በመሠረተ ልማት ግንባታ፣በማኀበራዊ ልማት፣በግብርና፣በቀጠናዊ ትስስር እና በኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አክሴል ቫን ትሮትሰንበርግ ጋር በሴኔጋል ዳካር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ የዓለም ባንክ አካል የሆነው እና አፍሪካ በምታገግምበት ሁኔታ ላይ ድጋፍ የሚሰጠው የዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር (በአይ.ዲ.ኤ 20) የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ሴኔጋል ዳካር ገብተዋል።

በዛሬው ዕለትም ከዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አክሴል ቫን ትሮትሰንበርግ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይታቸውም ÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሮቹን ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የዓለም ባንክ እምነት እንዳለው ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

የዓለም ባንክ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በመሠረተ ልማት ግንባታ፣በማኀበራዊ ልማት፣በግብርና፣በቀጠናዊ ትስስር እና በኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ላይ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

የዓለም ባንክ በኢኮኖሚ ላላደጉ አገራት ከመደበው 93ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ውስጥ 66 ቢሊየን ለ39 የአፍሪካ አገራት የመደበ ሲሆን÷ ከዚህም ውስጥ ለኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት 5 ነጥ 7 ቢሊየን ለመስጠት ቃል ገብቷል።

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሰላም ሂደት እና የተጀመረው የመልሶ ማቋቋም ግንባታ ጥረቶች በቋሚነት እንደሚደግፍ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አንስተው÷ በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት እና አወንታዊ እርምጃዎች በተመለከተ ገለጻ አድርገውላቸዋል ።

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ደመቀ÷ ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙም ግብዣ አቅርበውላቸዋል ።

በውይይቱ ላይ በቅርቡ የተሾሙት የባንኩ የምሥራቅ እና ደቡባዊ የአፍሪካ ቀጠናዊ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ የተገኙ ሲሆን÷ አቶ ደመቀ መልካም የሥራ ጊዜ ተመኝተውላቸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.