Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የግንባታ ውል የገቡ ተቋራጮች ሥራቸውን በጊዜ እንዲያጠናቅቁ ም/ከንቲባው አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ የፕሮጀክቶች ግንባታ ውል የፈጸሙ የሥራ ተቋራጮች ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲያጠናቅቁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ አሳሰቡ፡፡
አቶ ጃንጥራር ዓባይ በግንባታ ሥራዎች ዙሪያ ከስራ ተቋራጮች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ተቋራጮች በገቡት ውል መሰረት የተዋዋሉትን ስራ ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ውል ወስደው ግንባታ በማያጠናቅቁ ተቋራጮች ላይም በውል ስምምነቱ መሠረት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እና በሌላ ተቋራጭ እንደሚተካ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱም የሥራ ተቋራጮች በውላቸው መሰረት ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ እየሠሩ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
ተቋራጮች በበኩላቸው÷ አሁን ያለው የግንባታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ በስራቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው እና የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
በፊት ከነበረው የዋጋ ስምምነት ውጭ የዋጋ ማሻሻያ እንደማይደረግና ተቋራጮች አስፈላጊውን ዋስትና በማስያዝ ተገቢ ብድር እንደሚመቻችላቸው አቶ ጃንጥራር ማሳወቃቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
የኮንስትራክሽን ቢሮውም ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.